ሰልጣኞች የህግ አወጣጥና አተገባበር ላይ በንድፈ ሃሳብ እንዲሁም በተግባር ያገኙትን ስልጠና በመደመር በዘርፉ ውጤታማ ስራ መስራት እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገነዘበ

ሰልጣኞች የህግ አወጣጥና አተገባበር ላይ በንድፈ ሃሳብ እንዲሁም በተግባር ያገኙትን ስልጠና በመደመር በዘርፉ ውጤታማ ስራ መስራት እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገነዘበ

ምክር ቤቱ በወራቤ ዩኒቨርሲቲ 5ኛ አመት የህግ ተማሪዎች በህግ አወጣጥና ትግበራ ላይ ያተኮረ ስልጠና በወልቂጤ ከተማ ሰጥቷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ደምሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በሁለንተናዊ ዘርፎች ላይ አብሮ እንደሚሰራና ይህንኑ አጠናክሮ ይቀጥላል።

ይህንን ተከትሎ በምክር ቤቱ አዘጋጅነት በወራቤ ዩኒቨርሲቲ 5ኛ አመት የህግ ተማሪዎች በህግ አወጣጥና ትግበራ ላይ ያተኮረ ስልጠና መሰጠቱን የተናገሩት ሃላፊው፤ በዚህም ሰልጣኞቹ በህግ አውጪው ተቋም የወጡ ህጎች በተግባር ሲመለከቱ ክህሎታቸውን ይበልጥ ያጎለብተዋል ብለዋል።

በመሆኑም ሰልጣኞች የህግ አወጣጥና አተገባበር ላይ በንድፈ ሃሳብ እንዲሁም በተግባር ያገኙትን ስልጠና በመደመር በዘርፉ ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አቶ ዳዊት አስገንዝበዋል።

ስልጠናውን የሰጡት በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምክር ቤቱ የህግ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ያሲን ሳኒ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ሰልጣኞች ቀጣይ የማህበረሰቡ አገልጋይ እንደመሆናቸውና በዘርፉ ያላቸውን ክህሎት መጎልበቱ ለማህበረሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላቸዋል።

አስፈላጊ ሂደቶችን አልፈው የጸደቁ እና በክልሉ እየተተገበሩ ያሉ አዋጆችና ህጎች በሰነድ በተደገፈ መልኩ ተገባራዊ ስልጠና መሰጠቱን የተናገሩት አቶ ያሲን፤ ይህን ከግንዛቤ በማስገባት በዘርፉ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን በመቅረፍ ውጤታማ ስራ መስራት ከሰልጣኞች ይጠበቃል።

በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት አሰልጣኝ የሆኑት ኢንስትራክተር ሃይሩ ሱልጣን፤ ምክር ቤቱ ላደረገላቸው ጥሩ አቀባበል አመስግነው በቆይታቸውም ሰልጣኞች በተግባር በተመለከቱት ነገር ተጨማሪ እውቀት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል ሲሉም አስረድተዋል።

ከሰልጣኝ የ5ኛ አመት የህግ ተማሪዎች መካከል ነጻነት መስፍን፣ መሉነህ ለማ እና ፈሪሃ ሙሂዲን ይገኙበታል።

በሰጡት አስተያየትም በንድፈ ሃሳብ የተማሩት በተግባር መመልከታቸው እውቀታቸውን ይበልጥ እንደሚያጎለብተው ገልጸው በተለይም ወደ ስራው አለም ሲቀላቀሉ ሂደታቸውን ጠብቀው የወጡ ህጎችና አዋጆች በተገቢው እንዲተገበሩ በማድረግ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን