በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በጎፋና ባስኬቶ ሀገረ ስብከት የነበረው አለመግባባት በሰላም መፈታቱን ተከትሎ የእርቀ ሠላም ማጠቃለያ ኮንፈረንስ ተካሄደ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በጎፋና ባስኬቶ ሀገረ ስብከት የነበረው አለመግባባት በሰላም መፈታቱን ተከትሎ የእርቀ ሠላም ማጠቃለያ ኮንፈረንስ ተካሄደ

ሀዋሳ፡ ጥር 08/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በተገኙበት በጎፋና ባስኬቶ ሀገረ ስብከት ለስድስት ዓመታት ዘልቆ የነበረው አለመግባባት ቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፈውን የሰላም ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ የእርቀ ሠላም ማጠቃለያ ኮንፈረንስ በሳውላ ከተማ ተካሂዷል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ፤ ሰላም ለሰው ልጆች ሁሉ መንፈሳዊና ማህበራዊ አገልግሎት መሰረት በመሆኑ የተገኘውን ሰላም በማጽናት በመደጋገፍና በመተባበር ማህበራዊ ዕሴቶቻችንን በማጎልበት አንድነታችንን ማጠናከር ይኖርብናል ብለዋል።

በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ የዛሬው ቀን ፍቅር ያሸነፈበት ይቅርታና አብሮነት ከፍ ያለበት ቀን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ መሰረት የጣለ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

ግጭት በንግግርና በውይይት የመፍታት ልምዳችንን በማጠናከር አብሮነታችንን ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በቤተክርስቲያኒቱ የነበረው የጥል ግድግዳ በሰላማዊ መንገድ በፍቅር መቋጨቱ ለዘላቂ ሰላም ልማትና ዕድገት መሰረት ነው ብለዋል።

የሰላም ኮንፈረንሱ በአካባቢው የህዝብ ለህዝብ ትስስርና አብሮነት እንዲጠናከር እንዲሁም ልማት እንዲቀጥል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በኮንፈረንሱ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎት፣ ትምህርትና ቡራከ ሰጥተዋል።

በመድረኩ ለእርቀ ሰላሙ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ዕውቅና ተሰጥቷል።

በሰላም ኮንፈረንሱ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፣ በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌልና ሀዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የጋሞና አካባቢው የጎፋና ባስኬቶ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የፌዴራል፣ የክልል የሁለቱ ዞኖች ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት ፎረም አመራሮች እና የአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን