“ነገን ዛሬ እንትከል”

“ነገን ዛሬ እንትከል”

በደረጀ ጥላሁን

የደን ሃብት ከፍጡራን ጋር ያለው ቁርኝት ከፍተኛ ነው፤ ምንም እንኳን የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ ለተፈጥሮ አደጋና ድርቅ ቢያጋልጠንም፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ታዲያ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከፍተኛ ለውጥ እያስገኘ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ (ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ እስከ 2014) 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል አቅዳ ከ25 ቢሊዮን በላይ የተለያየ ጥቅም ያላቸው ዛፎች መትከል ችላለች፡፡ በዚህ መርሃ ግብር ከ25 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መሳተፋቸውና የጽድቀት መጠኑም በአማካይ 80 በመቶ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በሐምሌ 2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመጀመሪያው አመት ብቻ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኝ እንዲተከል በማድረግ እቅዱን ሙሉ በሙሉ ማሳካት ተችሏል፡፡ በመርሃ-ግብሩ በአንድ ቀን ብቻ 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ግብ የተቀመጠ ቢሆንም 354 ሚሊዮን ችግኝ መትከል መቻሉ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አድናቆትን አግኝቷል፡፡

የሁለተኛው ምእራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሰኔ 1/2015 ዓ/ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡ በዚህም በአራት ዓመት የሚተገበር 25 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ሥራው ተጀምሯል፡፡ በ2015 ዓ/ም ‹‹ነገን ዛሬ እንትከል›› በሚል መሪ ቃል 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኝ የሚተከል ይሆናል፡፡

እንደ ሀገር የሚተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በደቡብ ክልልም በተመሳሳይ ተጀምሯል፡፡ በዚህ መሠረት በ2ኛው ምእራፍ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ከ1 ቢሊዮን ችግኝ በላይ መዘጋጀቱን ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቦጋለ ሌንጫ ለ2ኛው ምእራፍ የአረንጓዴ አሻራ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በመስራት ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

በክልሉ በመጀመሪያው ምእራፍ ባሉት አራት ተከታታይ አመታት 5 ነጥብ 35 ቢሊዮን ችግኝ ተዘጋጅቶ 4 ነጥብ 23 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል፡፡ በዚህም 19 ሚሊዮን የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በመጀመሪያው ምእራፍ የአረንጓዴ አሻራ ውጤቶች ተመዝግበዋል ያሉት አቶ ቦጋለ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን መቋቋም እና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን መቀነስ ተችሏል ብለዋል፡፡ የተጎዳና የተመናመነ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ በረሀማነትና የአካባቢ መራቆት እንዲቀንስ አስችሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአፈር መሸርሸር፣ ጎርፍና ናዳ እንዲሁም የእንስሳት መኖ አቅርቦት እንዲሻሻልም ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ለኑሮ መሻሻል ከፍተኛ ድጋፍ የሚያደርጉ የተለያዩ የፍራፍሬ ዝርያዎች መተከላቸውን አመላክተዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በተሰራው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ የገፅና የከርሰ ምድር የውሃ አካላት እንዲጎለብቱና የብዝሃ ሕይወት ሀብት እንዲያድግ አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለደን ሽፋን መጨመር እና ለኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ችግኝ ለሚያመርቱ ወጣቶችና ሴቶች የተሻለ የገቢ እድል ፈጥሯል፡፡ ከዚህ አኳያ ለ52 ሺህ 934 ሰዎች የሥራ እድል መፈጠሩን እንዲሁም የለሙ ተፋሰሶችን ለወጣቶችና ለሴቶች በማስተላለፍ ለ16 ሺህ 190 ሰዎች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡

በክልሉ የተተከሉት በዋናነት የምግብ ዋስትና ክፍተትን ሊሞሉ የሚችሉ እና ተሸጠው ገቢ የሚያስገኙ እንደ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ እና ማንጎ የመሳሰሉት የፍራፍሬ ዓይነቶች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡

የጽድቀት መጠናቸውም ደግሞ ከ85 በመቶ በላይ ሲሆን በ2014 ዓ/ም በብዙ የክልሉ አካባቢዎች በተፈጠረው የዝናብ እጥርት እና ደረቃማ የአየር ሁኔታ መነሻ ግን እስከ 69 በመቶ ሆኖ ነበር፡፡

በ2ኛው ምእራፍ ጥራት ያላቸው ችግኞች ማፍላትና በሚሰጡ ሙያዊ ምክረ ሀሳቦች መሠረት ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ ከዚህ ሌላ ድርቅና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳያደርስ እርጥበትን መያዝ የሚያስችሉ ሥራዎችን ቀድሞ መስራት ይጠይቃል ብለዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ አርሶ አደሩ 30-40-30 በሚል በሶስት ዓመት ውስጥ 100 የፍራፍሬ ችግኞችን መትከል የሚያስችልም ነው ተብሏል፡፡

በክልሉ የዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሃ- ግብር በሚያዚያ ወር የተጀመረና እስካሁን 40 በመቶ የሚሆነው የተተከለ ሲሆን ቀሪው ደግሞ በቀሪ ጊዜያት ይተከላል፡፡

በሲዳማ ክልልም በተመሳሳይ ‹‹ነገን ዛሬ እንትከል›› በሚል መሪ ቃል እየተከናወነ ለሚገኘው የዘንድሮ መርሀ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው 306 ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትልና የተፈጥሮ ሀብት መሬት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍቅረኢየሱስ አሸናፊ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ ተከላው እየተካሄደ ሲሆን እስካሁን 50 በመቶ የሚሆነው ችግኝ እንደተተከለና ቀሪውን ለማሳካት ከሰኔ 9 ጀምሮ መጀመሩን አመላክተዋል፡፡

በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር  34 በመቶ የሚሆኑ ችግኞች የሀገር በቀል ዝርያዎች ሲሆኑ እነዚህን በጥምር ደን አልያም በተለያዩ ቦታዎች ለመትከል 32 ሺህ ሄክታር መሬት ተለይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ እንዲሁም ለእንስሳት መኖ የሚሆኑ ችግኞች እየተተከሉ ይገኛል ብለዋል፡፡

በሲዳማ ክልል በተካሄደው የመጀመሪያ ምእራፍ የአረንጓዴ አሻራ 850 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡ የጽድቀት መጠኑ በአማካይ 85 ነጥብ 4 በመቶ መሆኑን የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ እንደ ሀገር የተሻሻለ የግብርና አሰራር በማስፈን፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ የውሃ ሃብትንና የብዝሃ ህይወት ጥበቃን በማረጋገጥ ዘላቂ ተጠቃሚነትን ያስገኛል፡፡ በተጨማሪም የአለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የራሱን አስተዋጽኦ በማበርከት የካርቦን በካይ ጋዝን ለመቀነስ እንደሚረዳም ተገልጿል፡፡

መርሃ ግብሩ አስተማማኝ እንዲሆን የተተከሉ ችግኞችን በባለቤትነት ማስተዳደርና መንከባከብ ዘላቂ የሆነ የገቢ ምንጭ እንዲሆን በባለቤትነት መሥራት ተገቢ ነው፡፡