“እጄን ለልመና ከመዘርጋት ታድጎኛል”

“እጄን ለልመና ከመዘርጋት ታድጎኛል”

በደረሰ አስፋው

”ዕድልህን ስትጠቀም ብቻ ነው ህይወትህን የምትለውጠው፡፡ ማንኛውንም የስራ ዕድል ለመጠቀም ዝግጁ ካልሆንን ዕድሎች ይመጣሉ ነገር ግን እንዲሁ ያመልጡናል። ይህ የብዙዎቻችን ችግር በመሆኑ ለድህነት እንዳረጋለን በማለት ነው ንግግራቸውን የጀመሩት፡፡

ከሁኔታዎች ጋር መላመድና፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን የመቋቋም ችሎታ አዳብረዋል። የቤተሰብ ችግር፣ ባልታሰበ ጊዜ ከተከሰተ የአካል ጉዳት ጋር ተደማምሮ ጭንቀት ፈጥሮባቸዋል፡፡ በዚህም ችግርን የመቋቋም አቅምን አጎልብተዋል፡፡

ባደጉበት የትውልድ ቀያቸው እርፍ ጨብጠው ለማረስ ቢያዳግታቸውም ሌላ አማራጭ እንዳለ ይረዱ ነበር፡፡ ለዚህም መፍትሄ ወዳለበት መንቀሳቀስ እንጂ ያለፈ ታሪክ ማሰቡን አልመረጡትም፡፡ ለዛሬው የአርባ ምንጭ ነዋሪነታቸውም ምክንያቱ ይሄው ነው፡፡

አቶ ሳሙኤል ኤቸሌ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ የተወለዱት በወላይታ ዞን አረካ ዙሪያ ዶላ ቀበሌ ነው፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ከእድሜ እኩዮቻቸው ጋር ቦርቀውና ተጫውተው አድገዋል፡፡ እስከ 12 አመታቸው ድረስ ሙሉ አካል ነበራቸውና ትምህርታቸውን ከፊደል ቆጠራ አልፈዋል። ነገር ግን በድንገት ወድቀው ለአአካል ጉዳት ተጋለጡ፡፡ በቤተሰብ የኢኮኖሚ አቅም ማነስ ምክንያት ታክመው የመዳን ተስፋቸው ተመናመነ፡፡ ህመማቸው በርትቶ ለአካል ጉዳት አጋለጣቸው፡፡

ከአርሶ አደር ቤተሰብ የወጡት አቶ ሳሙኤል ከቤተሰቦቻቸው ይሄን ድጋፍ አገኛለሁ፤ ታክሜም እድናለሁ ብለው የሚያስቡት ነገር እንደሌለ ያውቁ ነበር። ችግር ሲደመር አካል ጉዳት በወቅቱ ለሳቸው ፈተና ነበር፡፡ የአሁኑ የአካል ድጋፍ በቀላሉ የሚገኝ ባለመሆኑ ችግራቸውም ቀጠለ። ነገር ግን እግራቸውን በእጃቸው እየደገፉ ቤተሰብን ስራ ከማገዝ አልተቆጠቡም፡፡

በእንዲህ ሁኔታ ላይ እያሉ አንድ የምስራች ወደ ጆሯቸው ገባ፡፡ በአርባ ምንጭ የአካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል ለችግራቸው መላ አለው የሚል፡፡ ጊዜም አልወሰደባቸው። ወደ አርባ ምንጭ አቅንተው ክራንች አገኙ። ለዚህም የአርባ ምንጭ የአካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከልን ያመሰግናሉ፡፡

ሁሉም ሰው ችግር ሊያጋጥመው እንደሚችል የሚናገሩት አቶ ሳሙኤል እኔ ግን ችግሩን እንዴት አልፈዋለሁ የሚለው ጠንካራ የስነ ልቦና ዝግጅት እንዳደርግ እድል ፈጥሮልኛል ይላሉ፡፡ አቶ ሳሙኤል “ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር እራስን ማላመድ ወደፊት ለምናደርገው ነገር ትልቅ ስንቅ ነው” ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

እጅን ለልመና ከመዘርጋት ይልቅ አማራጭ የስራ ዘርፎችን መቃኘት ጀመሩ፡፡ “ማደግ ከፈለግህ እራስህ የመፍትሄው ሰው ሁን” የሚሉት አቶ ሳሙኤል አንድ ሰው ለስኬት የሚያበቃው አስተሳሰብ ነው የሚል አመለካከት አላቸው፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ 16 ዓመታትን የኖሩት አቶ ሳሙኤል በአካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል የሚያገኙት ድጋፍም እየተሻሻለ መምጣቱን ያወሳሉ፡፡ ከክራንች በተጨማሪ ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ ስለተገጠመላቸው እንደልብ ለመንቀሳቀስና ለመስራትም ችለዋል፡፡ ይህም ዛሬ ላይ ለደረሱበት ደረጃም አብቅቷቸዋል፡፡

አቶ ሳሙኤል በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ በተለያዩ የስራ መስኮች በመሰማራት እራሳቸውን እየደገፉ ይገኛሉ፡፡ የሊስትሮ ስራውም የነበረባቸውን ችግር የሚያቃልል ሆነ፡፡ የተሻለ ኑሮን ለመምራት ዕድል ፈጠረላቸው፡፡ ለቀጣይ ውጥናቸውም በር ከፈተ፡፡ በዚህም ለመለወጥና ለማደግ ያላቸው ፍላጎትንም አሳደገ፡፡

ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ እንደሚባለውም ችግራቸውን ለመጋራት ፈቃደኛ ከሆነች ሴት ጋርም ትዳር መሰረቱ። ባለቤታቸውም አካል ጉዳተኛ ነህ ከሚል ፊት ከመንሳት ይልቅ ተደጋግፎ ማደግና ለመለወጥ መምረጣቸውን ያደንቃሉ፡፡ ከጎናቸው ሆነው ሻይ ቡና መስራታቸው ትዳራቸው ፍሬ እንዲያፈራ ማገዙን በማስታወስ፡፡ ልጆቻቸው በግል ትምህርት ቤት እየከፈሉ ያስተምራሉ፡፡

የገቢ ምንጫቸው የሊስትሮ ሥራ ሲሆን ስራው ከልመና እንድወጣ አግዞኛል ይላሉ፡፡ አቶ ሳሙኤልን በስራ ቦታቸውም ከጧት እስከ ማታ ይቆያሉ፡፡ “ጤነኛ ሆኜ ከስራ ውጭ ሆኖ መቀመጥ ለኔ እንደሞት ነው” ብለውም ይናገራሉ፡፡

ከሊስትሮ ስራ ጎን በማታው መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ለመከታተል ሞክረዋል። ምንም እንኳን መቀጠል ባይችሉም። አሁን ላይ የኑሮው ሁኔታ ከበድ ሲልባቸው ወደ ስራው በማተኮር የቤተሰባቸውን ህይወትም ይደግፋሉ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጀላቸው የመስሪያ ቦታ ከጫማ ማሳመር እስከ ማ ደስ ስራም ጀምረዋል፡፡

በአንድ በጎ አድራጎት ድርጅት በቆዳ ስራ ላይ የወሰዱት ስልጠናም አሁን ለተሰማሩበት የጫማ ማደስ ስራ ክህሎት የፈጠረላቸው አቶ ሳሙኤል በበርካታ ደንበኞቻቸው ዘንድ ተመራጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም “በርታ” የሚባል ማህበር መስርተው ቢደራጁም በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ለመስራት ግብአት ባለመኖሩ ለመበተን መገደዳቸውን በመጠቆም፡፡

“የአቅም ጉዳይ አስሮ ይዞኝ እንጂ ከሊስትሮ ስራው በተጨማሪ በጫማ፣ ቀበቶና ቦርሳ ስራ መሰማራት እችል ነበር፡፡ ለስራው የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ማግኘት ባለመቻሌ በሊስትሮ ብቻ እንድወሰን አድርጎኛል፡፡ ይህም ቢሆን አልከፋኝም፡፡ ጥሩ የሚባል የገቢ ምንጭ ሆኖኛል፡፡ እጄን ለልመና ከመዘርጋት ታድጎኛል” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠው ድጋፍ አነስተኛ በመሆኑ እንጂ ከዚህ የተሻለ ህይወትን መምራት እንደሚችሉም ያነሳሉ። አካል ጉዳተኞች ለልመና እንደተፈጠሩ አድርጎ የመመልከት አስተሳሰብ ዛሬም አለመገታቱን የሚያነሱት አቶ ሳሙኤል፡፡ የሚብሰው ደግሞ ተማሩ በተባሉ አካላት መሆኑ የጉዳዩን አሳሳቢነት ያሳያልም ብለዋል፡፡

ዛሬ ላይ አቶ ሳሙኤል የአካል ጉዳተኞች ህመም እና ስቃይ የኔም ህመምና ስቃይ ነው በማለት አካል ጉዳተኞች ከጓዳ ወጥተው እራሳቸውን እንዲችሉ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡ ቤተሰብ አካል ጉዳተኛ ልጆችን ለጉልበት ብዝበዛ እንዳይጠቀምባቸው የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

ከዚህም አንፃር አንድ የአካል ጉዳተኛ ከወላይታ አካባቢ በማምጣት እራሱን እንዲችል ያደረጉትን ያነሳሉ፡፡ ወደ አርባ ምንጭ በማምጣት የአካል ድጋፍ አግኝቶ የመማር እድልም እንዲያገኝ አድርገዋል። “ነገ ይሄ ልጅ ተምሮ ለቁም ነገር ሲደርስ አይቶ ከመደሰት የሚልቅ ነገር የለም” ሲሉም ቀጣይ አካል ጉዳተኞች የተሻለ ህይወት እንዲመሩ በበጎ ስራ ላይ ለመሰማራት እቅድ እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡

የሰራ ሰው የእለት ጉርሻ አያጣም የሚሉት አቶ ሳሙኤል ከቤት የተደበቁትን በማውጣት ቡሩሽ እየሰጡ ሊስትሮ ስራ ላይ እንዲሰማሩ የማድረግ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት አስበዋል፡፡ ለዚህም ቀድመው ከቤት እንዲወጡ ማድረግ ይገባል ባይ ናቸው፡፡ እስካሁንም ሀሳብ በማመንጨትና ልምዳቸውን በማጋራት በርካታ አካል ጉዳተኞች ከልመና ወጥተው መለወጥ እንዲችሉ ማድረጋቸውንም ነው የተናገሩት።

አቶ ሳሙኤል አሁን ባሉበት የስራ መስክ ብቻ ተወስነው የመቅረት ዓላማ የላቸውም። የተለያዩ ማሽኖችን በማምጣት የጫማ ማደሻ ለመክፈት አቅደዋል፡፡ “የኑሮ ወድነቱ እያየለ ባለበት በዚህ ወቅት የገቢ ምንጭህንም አብረህ ማሳደግ ካልቻልክ ችግሩ ሊጫንህ ይችላል” በሚል የስራ አድማሳቸውን ለማስፋት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እቅዳቸው እውን ይሆን ዘንድ የእኛም ምኞት ነው፡፡