በ31 ተከታታይ ጨዋታዎች ያልተሸነፈው ብሔራዊ ቡድን
የስፔን ብሔራዊ ቡድን በ31 ተከታታይ ጨዋታዎች ባለመሸነፍ አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቧል።
የወቅቱ የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊው ብሔራዊ ቡድን በመለያ ምት የተሸነፈባቸውን ጨዋታዎች ሳይጨምር ነው እዚህ የጨዋታ ቁጥር ላይ መድረስ የቻለው።
በአሰልጣኝ ሉይዝ ዴላፎንቶ የሚመራው የስፔን ብሔራዊ ቡድን በአውሮፓ ዙር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያም በምድቡ ምንም ጨዋታ ሳይሸነፍ በቀጥታ ወደ ዓለም ዋንጫው ተሻግሯል።
ላሮጃዎቹ ትናንት ምሽት የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታቸውን በሜዳቸው ከቱርክ ጋር አከናውነው 2 አቻ በሆነ ውጤት አጠናቀዋል።
በላ ካርቱጃ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ለስፔን ጎሎች ዳኒ ኦልሞ እና ሚኬል ኦያርዛባል አስቆጥረዋል።
ለቱርክ ደግሞ ዴኒዝ ጉል እና ሳሊህ ኦዝካን ጎሎችን አስገኝተዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ስፔን ከምትገኝበት ምድብ ስድስት 16 ነጥቦችን በመያዝ ምድቧን በቀዳሚነት አጠናቃ ወደ 2026 የዓለም ዋንጫ በቀጥታ አልፋለች።
የ2010 የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮኗ ስፔን ለ17ኛ ጊዜ ነው ወደ ዓለም ዋንጫ የተሻገረችው።
ስፔን ከ1978 የሜክሲኮው የዓለም ዋንጫ ወዲህ በ13 ተከታታይ የዓለም ዋንጫ የተሳተፈች ሲሆን ከጀርመን በመቀጠል በተከታታይ የዓለም ዋንጫዎች በመሳተፍ 2ኛዋ አውሮፓዊት ሀገር ሆናለች።
የአራት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ጀርመን 1950 የብራዚሉ የዓለም ዋንጫ አንስቶ በ19 ተከታታይ የዓለም ዋንጫ በመሳተፍ ቀዳሚ ነች።
አሰልጣኝ ሉይዝ ዴላ ፎንቴ በ31 ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈትን ያላስተናገደ ቀዳሚው የስፔን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ይገኛሉ።
ዴላ ፎንቴ በቀድሞ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ቪንሴንቴ ዴልቦስኬ በ29 ጨዋታዎች ባለመሸነፍ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን ነው በእጃቸው ያስገቡት።
ስፔን በአሰልጣኝ ሉይዝ ዴላ ፎንቴ መሪነት በ2023 በኔሽንስ ሊግ በጣሊያን ከተሸነፈች ወዲህ በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እስካሁን ሽንፈትን አላስተናገደችም።
በእነዚህ ጊዚያት ውስጥ ስፔን 25 ጨዋታዎችን በድል ስታጠናቅቅ በ6 ጨዋታዎች ደግሞ ከተጋጣሚዎቿ ጋር አቻ ተለያይታለች።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
የወጣቶችን አካላዊና አዕምሮዊ ጤና ለመጠበቅ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
ጋብርኤል ማርቲኔሊ በ5 ተከታታይ የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ጎል ያስቆጠረ የመጀመሪያው የአርሰናል ተጫዋች ሆነ
ጆሿ ዚርኪዜ በሮማ ይፈለጋል