ወደ ዓለም ዋንጫው ለበርካታ ጊዜ በማለፍ ከብራዚል በመቀጠል ሁለተኛው ሀገር

የ4 ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ጀርመን ወደ 23ኛው የዓለም ዋንጫ በቀጥታ ማለፏን አረጋግጣለች።

በአሰልጣኝ ጁሊያን ናግሊስማን የሚመራው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በአውሮፓ ዞን የዓለም ዋንጫ ምድብ ማጣሪያ የመጨረሻ ዙር መርሐግብር ስሎቫኪያን 6ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ነው ወደ ዓለም ዋንጫው መሻገሩን ያረጋገጠው።

ትናንት ምሽት በሬድ ቡል አሬና ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ለጀርመን የማሸነፊያ ግቦችን ሌሮይ ሳነ ሁለት ጎሎችን አስቆጥሯል።

ኒክ ቮልትማደ፣ ሰርጂ ግናብሪ፣ ራይድል ባኩ እና አሳን ኦድራኦጎ ቀሪ ጎሎችን ከመረብ አሳርፈዋል።

ጀርመን ማሸነፏን ተከትሎ ነጥቧን 15 በማድረስ ምድብ አንድን ቀዳሚ ሆና በማጠናቀቅ በቀጥታ ወደ 2026 የዓለም ዋንጫ አልፋለች።

በ12 ነጥብ 2ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ስሎቫኪያ በበኩሏ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅላለች።

ጀርመን ወደ ዓለም ዋንጫው ለበርካታ ጊዜ በማለፍ ከብራዚል በመቀጠል ሁለተኛው ሀገር ሆናለች።

የ5 ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ብራዚል ሁሉንም (23) የዓለም ዋንጫዎች ማለፍ በመቻል ብቸኛዋ ሀገር ስትሆን ጀርመን 21 ጊዜ ወደ ዓለም ዋንጫ በማለፍ ተከታዩን ደረጃ ይዛ ትገኛለች።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ