የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት በእንስሳትና ንብ ማነብ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ኑሮአቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ገለጹ

የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት በእንስሳትና ንብ ማነብ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ኑሮአቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ገለጹ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 07/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ ሹርሞ ዊጥቢራ ቀበሌ የሚገኙ ሞዴል አርሶአደሮች በጥምር ግብርና የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት በእንስሳትና ንብ ማነብ ዘርፍ በመስራታቸው ኑሮአቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ተናገሩ።

በወረዳው ከምግብ ተረጂነት ለመውጣት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ ኢንሼቲቮችን ተግባራዊ በማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት አስታውቋል።

በዞኑ ሌሞ ወረዳ ሹርሞ ዊጥቢራ ቀበሌ ሞዴል አርሶአደር የሆኑት ተሻለ መንዴራ ባለቸው ይዞታ ከመደበኛ አዘዕርት ሰብሎች በተጨማሪ ጥቅል ጎመን፣ ካሮት፣ ቲማቲም ፣ሽንኩርት እና የመሳሳሉ የጓሮ አትክልቶችንና ልዩ ልዩ የፍራፍሬ ዛፎችን በመትከል ውጤታማ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

በተጨማሪ ንብ በማነብ፣ እንስሳት፣ ዶሮ በማርባት ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት አርሶአደሩ÷ ለዚህም መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ግብዓቶችንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ እያገዟቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሌላኛው በቀበሌው ሞዴል አርሶአደር የሆነው ወጣት እሸቱ አባተ በበኩሉ ከቤተሰቡ ጋር በመሆን እያከናወኑት በሚገኙ የተለያዩ የግብርና ስራዎች ከጥቂት ምርቶች ውጭ ከገበያ እንደማይሸምቱና አብዛኛውን ምርቶች ከጓሮኣቸው እንደሚጠቀሙ ተናግሯል ።

ከጥቅት ዓመታት በፊት ሁለት የተሻሻሉ ላሞች የጀመረው የወተት ምርት በአሁኑ ወቅት በቀን ከ90-100 ሊተር እንደሚያቀርቡና የላሞችም ቁጥር 16 መድረሱን አክሏል ።

ከተለያዩ ሰብሎችና የጓሮ አትክልቶች ጎን ለጎን የተሻሻሉ የከብቶች መኖ በማምረት ለውጤታማነቱ እንዳገዛቸው አርሶአደሩ ገልጿል ።

መንግሥት ለግብርና ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት አርሶአደሮች ባለመሰልቸት የተሻለ በማምረት ከራሳቸው አልፈው ለገበያ በስፋት ምርቶችን ለማቅረብ መስራት እንደሚጠበቅባቸው የተናገሩት ሞዴል አርሶአደሮቹ ልምዳቸውንም ለማጋራት መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

በሀዲያ ዞን የሌሞ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰልፋሞ ወ/ዮሐንስ በወረዳው በሚገኙ 28 የገጠር ቀበሌያትና 3 ታዳጊ ማዘጋጀዎች የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ የሆኑ የሌማት ትሩፋት፣ 30 40 30 የተሰኙ ኢንሼቲቭ የግብርና ስራዎች ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።

በንብ ማነብ እና በዶሮ እርባታ በሌሎችም መንደሮችን በመለየት በትኩረት እየተሰራ ሲሆን በንብ ማነብ ዘርፍ ከባህላዊ ወደ ዘመናዊ ቀፎ እንዲሻገሩ እንዲሁም አንድ አርሶአደር ቢያንስ 5 የእንቁላል ዶሮች በቤቱ እንዲያረባ በፕሮጀክቶች ትብብር እና በመንግሥት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ከተረጂነት ለመውጣት የወተትና ስጋ ምርትን ለመጨመር የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን በማቅረብና በማዳቀል የእንሰሳት ጤና መጠበቅና የተሻሻሉ መኖዎችን እንዲመገቡ ማድረግ በአሁኑ ወቅት የትኩረት አቅጣጫዎች መሆኑን አቶ ሰልፋሞ ተናግረዋል ።

ወረዳው ለሆሳዕና ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ እንደመገኘቱ መጠን ይህንን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የምርቶችን አቅርቦቱ ከፍ ለማድረግ በቀጣይ ግብርናን በማዘመንና በትኩረት እንደሚሰራ ኃላፊው ገልፀዋል።

ዘጋቢ: ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን