በክልሉ የትምህርት ጥራት፣ ውጤትና ተደራሽነት ዙሪያ ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ

በክልሉ የትምህርት ጥራት፣ ውጤትና ተደራሽነት ዙሪያ ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ

ቢሮው መንግስት በትምህርት ልማት ከሚሠራው በተጨማሪ ከልማት አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ለተሻለ ውጤት እየሠራ መሆኑን የገለፁት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ታምራት ይገዙ ናቸው።

ቢሮው በትምህርት ጥራት፣ ተሳትፎና በልዩ ፍላጎት ዙሪያ የሚሰሩ ከዩኒሴፍ እና ከኖርዌይ የመጡ አካላትን ተቀብሎ በጉዳዩ ዙሪያ የጋራ ውይይትና መስክ ምልከታ መካሄዱን ዶ/ር ታምራት አስረድተዋል።

የኖርዌ ኦስሎ ድጋፍ የሚሰጡ አካላት ከዩኒሴፍ ጋር በመቀናጀት በክልሉ ስር በ12 ዞኖች በትምህርት ልማት እየሠሩ እንደሚገኙ ሀላፊው በዚህን ወቅት ገልፀዋል።

ልዩ ፍላጎት ለሚሹ ተማሪዎችም የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎችን የመንግስት የልማት አጋር አካላት ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን የተናገሩት ኃላፊው፤ ይህንን የተመለከተ መስክ ምልከታ በደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ ተካሂዷል ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ልማት ዕቅድ ስር የዩኒሴፍ በትምህርት ፕሮግራም ቴክኒካል አማካሪ አቶ ፍቅሬ ወ/ዮሐንስ እንደገለፁት፤ ዩኒሴፍ በክልሉ ስር ከመንግሥት ጎን በመቆም በትምህርት ልማት እየሠራባቸው ያሉ አካባቢዎች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

ይህንን በተለያየ ጊዜ በሚደረግ ድጋፋዊ ክትትል ወቅት ማረጋገጥ መቻሉን አቶ ፍቅሬ ተናግረዋል።

በደቡቡ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ ድጋፉን ካገኙና ጉብኝት ከተደረገባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ ኤሪያ ቃያሳ ሲሆን አጠቃላይ የትምህርት ልማት ሥራ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጉብኝቱን ያካሄዱ አካላት አረጋግጠዋል።

የአካባቢው አርብቶ አደሮችም መንግስት እየሠራ ካለው በተጨማሪ የልማት አጋር አካላት ድጋፍ ይበልጥ ሴት ልጆቻችንን እንድናስተምርና ልዩ ፍላጎት የሚሹ ልጆቻችንም ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ አቅም ፈጥሮልናል ብለዋል።

በአካባቢው የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችም በትምህርት ልማት ሥራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድር በክልሉ ትምህርት ቢሮ በኩል ትኩረት መድረጉም ተገልጿል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን