ከ2 ሺህ በላይ አዲስ ሰልጣኞችን ተቀብሎ ለማሰልጠን መታቀዱን የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቃ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 25/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2018 የስልጠና ዘመን እንደ ሀገር የአከባቢን ፀጋ ታሳቢ በማድረግ ከ2 ሺህ በላይ አዲስ ሰልጣኞችን ተቀብሎ ለማሰልጠን መታቀዱን የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቃ።
ከመደበኛ ስልጠና ጎን ለጎን ከ20 ሺህ በላይ የአጫጭር ጊዜ ሰልጣኞችን ተቀብሎ በማሰልጠን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት የማብቃት ስራ እንደሚሰራ ተመላክቷል።
በኮሌጁ የ2018 የስልጠና ዘመን ስራ ከመጀመሩ አስቀድሞ የመማሪያ ክፍሎች፣ የስልጠና ወርክሾፖችና የግብአት አቅርቦት ስራዎች እንዲሟሉ በማድረግ ከ2 ሺህ በላይ ነበር ሰልጣኞችን በመቀበል ስልጠና መጀመሩን የኮሌጁ ዲን አቶ አወል ሸንጎ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ2 ሺህ እስከ 3 ሺህ የሚደርሱ አዲስ ሰልጣኞችን እንደ ሀገር የአካባቢዎቹን ፀጋ ከግምት በማስገባት በኮንስትራክሽን፣ በግብርና፣ በውሃ ዘርፍና በሌሎችም የስልጠና መስኮች ተቀብሎ ለማሰልጠን በቴክኖሎጂ የታገዘ የOnline ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ከኮሌጁ በተለያዩ የሙያ መስኮች ሰልጥነው የወጡ ሰልጣኞች በግልም ሆነ በማህበር ተደራጅተው በመስራት ውጤታማ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ አወል፥ በተለይ የዘንድሮ አዲስ ተመዝጋቢ ሰልጠኞች እንደ አከባቢው በተለዩ የስልጠና ዘርፎች ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ አስረድተዋል።
ኮሌጁ ለአካል ጉዳተኛ ሰልጣኞች ከክፍያ ነፃ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑንም አቶ አወል አስታውቀዋል።
ኮሌጁ ከመደበኛ ስልጠና ጎን ለጎን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት በተለያዩ ዘርፎች የአጫጭር ጊዜ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ የተናገሩት ዲኑ፥ ባለፈው አመት 13 ሺህ ሴቶች ወደ ውጭ ሀገራት ለስራ ስምሪት ከመሄዳቸው አስቀድመው ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁመው ዘንድሮም ከ20 ሺህ በላይ ሰልጣኞችን ለማሰልጠን መታቀዱን ገልጸዋል።
ከኮሌጁ አሳልጣኞች መካከል ብሩክ አምባውና ረድኤት ፈለቀ በበኩላቸው ወደ ኮሌጁ የሚመጡ ሰልጣኞች በቂ እውቀት አግኝተው እንዲወጡ ለማድረግ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
በኮሌጁ የ3ኛ አመት የፋሽን ዲዛይን ሰልጣኝ የሆነችው ፍሬሕይወት በቀለ እና የአይሲቲ የ3ኛ ዓመት ሰልጣኝና አካል ጉዳተኛ የሆነችዉ ፀሐይ ወልዴ በሰጡት አስተያየት በኮሌጅ በሚገኙ ወርክሾፖች የተደራጀ የስልጠና ግብአት ተሟልቶላቸው በቂ እውቀት እያገኙ ስለመሆናቸው ገልጸዋል።
ኮሌጁን ለመጀመሪያ ጊዜ ከተቀላቀሉ አዲስ ሰልጣኞች መካከል ብሌን አዲሴና መብራቴ ደጉ እንዳሉት በኮሌጁ በተደረገላቸው አቀባበል ደስተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው በቀጣይ በመረጡት ዘርፍ ተገቢውን ሙያ ቀስመዉ በመውጣት ራሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን ለመጥቀም ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ዘጋቢ : ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የህፃናት የወደፊት የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻልና የተሻለ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመገንባት እየሠራ እንደሚገኝ የጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ ልማት ድርጅት ገለፀ
5ኛው አገራዊ የሠላም ኮንፈረንስን በተመለከተ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተላለፈ መልዕክት
ፈጣን ፣ ወቅታዊ እና ተአማኒ መረጃን ተደራሽ ለማድረግ ዘመኑን የሚመጥን አሰራርን መዘርጋት እንደሚገባ ተገለጸ