በሴቶች ላይ የሚደርሱ ማህበራዊ ጫናዎችን ለመከላከል የኢኮኖሚ ባለቤት እንዲሆኑ ለማስቻል ሁሉም ባለድርሻ አካላላት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሴቶች ላይ የሚደርሱ ማህበራዊ ጫናዎችን ለመከላከል የኢኮኖሚ ባለቤት እንዲሆኑ ለማስቻል ሁሉም ባለድርሻ አካላላት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ሰዎች ለሰዎች ድርጅት ገለፀ።
በሰዎች ለሰዎች ድርጅት የጎፋ የተቀናጀ የገጠር ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ፍሰኃ አስመላሽ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት በተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እንደገለጹት፥ በወረዳው፣ በግብርና፣ትምህርት ጤና እና ሌሎች የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ማህበራዊ ዘርፎች እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ሴቶችና ሕፃናት በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለተለያዩ ጥቃቶች ተጋላጭ በመሆናቸው ጥቃቱን ለመከላከል ሁሉም አካላት ሃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አስረድተዋል።
የሴቶችን መብት የሚፈታተኑ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተወግደው ዘላቂ ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ድርጅቱ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በጎፋ ዞን ደምባ ጎፋ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አራሹ አበበ ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ዘረፈ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ችግሮቻቸውን ለመፍታት በንቅናቄ የተደገፉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስራት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በወረዳው በማህበራዊና ኢኮኖሚያው ዘርፎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።
የደምባ ጎፋ ወረዳ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ፋናዬ ሀላጫ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ማስቀረትና መቃወም ሰብአዊ ግዴታችን ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።
በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች የሰው ልጆች መብት የሚቃረኑ ድርጊቶች ከመሆናቸው ባለፈ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን እንደሚያስከትሉ አስረድተዋል።
ያነጋገርናቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያዬት በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሚያስከትሉት ስነልቦናዊና አካላዊ ጥቃት ከፍተኛ በመሆኑ በተቀናጀ መልኩ ለመከላከል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
በኮሪደር ልማት፣ የመንገድ ግንባታ እና ተያያዥ ስራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ የጠቅላላ ተቋራጮች እና የአገልግሎት ተቋማት ትጋትና ቁርጠኝነት የሚበረታታ መሆኑ ተገለጸ
ትምህርት ቤቶች የዉስጥ ገቢያቸዉን በማሳደግ የግብዓት ችግሮችን በመቅረፍ ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢን መፍጠር እንዳለባቸዉ ተገለፀ
የሣውላ ከተማ ህዝብ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን አካሄደ