ትምህርት ቤቶች የዉስጥ ገቢያቸዉን በማሳደግ የግብዓት ችግሮችን በመቅረፍ ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢን መፍጠር እንዳለባቸዉ ተገለፀ

ትምህርት ቤቶች የዉስጥ ገቢያቸዉን በማሳደግ የግብዓት ችግሮችን በመቅረፍ ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢን መፍጠር እንዳለባቸዉ ተገለፀ

‎በአሪ ዞን ዎባ አሪ ወረዳ ትምህርት ቤቶችን የግብርና ሞዴል በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘዉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የወረዳዉ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታዉቋል፡፡

‎የዎባ አሪ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤልያስ ባንዳ፤ በወረዳዉ ባሉ 27 ትምህርት ቤቶች ያሏቸዉን የመሬት ሀብት በአግባቡ በመጠቀም የተለያዩ ቋሚና ጊዜያዊ ሰብሎችን በማምረት የመንግስትን ድጋፍ ከመጠበቅ ይልቅ በራስ አቅም ግበዓቶችን በማሟላት ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢን በመፍጠር ደረጃቸዉን እንዲያሻሽሉ ለማድረግ እየተሰራ ነዉ ብለዋል፡፡

‎ትምህርት ቤቶችን የግብርና ሞዴል ማድረግ የዉስጥ ገቢን ከማሳደጉ ባሻገር ለተማሪዎችም ሆነ ለማህበረሰቡ የባለቤትነት ስሜትን የሚፈጥር በመሆኑ ትምህርት ቤቶች እንደየአካባቢዉ ሁኔታ በሰብል ልማትም ሆነ በእንስሳት እርባታ ስራ ላይ ተሰማርተዉ የዉስጥ ገቢያቸዉን እንዲያሳድጉ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ኃላፊዉ ተናግረዋል፡፡

‎የዉብሐመር መጀመሪያና መካከልኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዋና ርዕሰ መምህር ኢዩኤል ዳንካና የቦይካ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ማሙሽ ገልሦ በጋራ፤ ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢን ለመፍጠር መምህራን፣ ተማሪዎችንና ህብረተሰቡን በማሳተፍ የትምህርት ቤቱን ገቢ ለማሳደግ የተለያዩ የሰብል አይነቶች ቡና ኮረሪማ በቆሎ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‎የዎባ አሪ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢሻዉ መካሪ በበኩላቸዉ፤ ምርታማነትን ለማሳደግ ትምህርት ቤቶችን የግብርና ሞዴል ለማድረግ በግቢያቸው ውስጥ ያሉ መሬቶችን በአግባቡ በመጠቀም ገቢ ማመንጨት እንዲችሉ ለማድረግ ግንዛቤ በመፍጠር ስራዎች እየተሰሩ ነዉ ብለዋል፡፡

‎ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን