የደመወዝ ማሻሻያውን ምክንያት በማድረግ ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ንግድ ቤቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ በዳውሮ ዞን የዋካ ከተማ አስተዳደር ንግድ ዩኒቲ አስታወቀ

የደመወዝ ማሻሻያውን ምክንያት በማድረግ ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ንግድ ቤቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ በዳውሮ ዞን የዋካ ከተማ አስተዳደር ንግድ ዩኒቲ አስታወቀ

‎የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪዎች በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ የወቅቱን የደመወዝ ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋደዎች የሚገኙ ከሆነ ለሚመለከተው አካል ለመጠቆም ዝግጁ ስለመሆናቸው አስታውቀዋል፡፡

‎በከተማው ባለው የንግድ እንቅስቃሴ በተመጣጣኝ ትርፍ ንግዳቸውን በመልካም ሁኔታ የሚያሳልጡ ነጋዴዎች እንደመኖራቸው መጠን በተቃራኒው ደግሞ የራሳቸውን ትርፍ ለማግበስበስ ሲሉ ብቻ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆነ ነው በከተማ አስተዳደሩ የንግድ ዩኒቱ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ግርማ ወንድማገኝ የሚናገሩት።

‎አስተባባሪው አክለውም ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ፣ ምርት የሚሰውሩና የዋጋ ዝርዝር የማይለጥፉ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች በከተማ አስተዳደሩ መኖራቸውን ገልፀው እነዚህም ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።


‎ከዚሁ ጋር ተያይዞ የፀጥታ አካላትን ያካተተ ግብረ-ሃይል በማቋቋም በከተማ አስተዳደሩ የገበያ ክትትልና ቁጥጥር ሥራ እየተሰራ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

‎እየተደረገ ባለው ክትትልና ቁጥጥርም በአንዳንድ አጥፊዎች ላይ አስተማሪ እርምጃዎችን በመውሰድ ከተማ አስተዳደሩ የግብይት ሂደቱ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል ለማስቻል እየተሰራ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

‎የከተማ አስተዳደሩ ፋይናንስ፣ ገቢና ንግድ ክላስተር አስተባባሪ የሆኑት አቶ መንግሥቱ ማሞ በበኩላቸው፤ የመንግሥት የሠራተኞችን ደመወዝ ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ እና ወቅታዊ የዋጋ ዝርዝርን ለሸማቹ ህብረተሰብ በግልፅና በሚታይበት ቦታ ባልለጠፉት ንግድ ቤቶች እና ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እየወሰድን እንገኛለን ብለዋል።

‎በከተማው ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል የተዋቀረው ግብረ-ሃይል ባደረገው ቁጥጥርና ክትትል በከተማ አስተዳደሩ ወደ ሃምሳ የሚደርሱ ህገ-ወጥ የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውንና የዋጋ ዝርዝርን እንዲሁ ባልለጠፉ በርካታዎች ላይ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተናግረዋል።

‎በመጨረሻም የፋይናንስ፣ ገቢና ንግድ ክላስተር አስተባባሪው ሸማቹ ህብረተሰብ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ በተለይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን የሚያደርጉ፣ የወቅቱን የገበያ ዋጋ ዝርዝር በግልፅ ቦታ የማይለጥፉና ዕቃዎችን የሚሰውሩ ነጋዴዎች የሚያጋጥሙ ከሆነ ጥቆማ እንዲያደርግ ሲሉም አሳስበዋል።

‎በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው በርካታ የከተማው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ ነጋዴዎች ለትርፍ መስራታቸው አግባብነት ያለው መሆኑን በመግለፅ ቢሆንም በወቅቱ የተደረገውን የደመወዝ ማሻሻያ ብቻ ምክንያት በማድረግ የሚፈጠርና ተያይዞም እየተፈጠረ ያለው የዋጋ ጭማሪ አግባብነት የሌለውና አልፎም ተርፎ ጉዳዩ ሸማቾችን ብቻ ሣይሆን አካባቢን ጭምር የሚጎዳ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

‎አሁን ከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ያለው ክትትል፣ ቁጥጥርና እርምጃም ተገቢ እንደሆነ የገለፁት ነዋሪዎቹ፤ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ከሆነም በዚሁ ጥቆማን በመስጠት ለመተባበር ዝግጁ ስለመሆናቸው አስታውቀዋል።

‎ዘጋቢ: አሸናፊ ግዛው – ከዋካ ጣቢያችን