በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከ35 ሺህ 4 መቶ ሄክታር በላይ የተጎዱ መሬቶችን በአርሶ አደር መር የተፈጥሮ ሀብት ማገገሚያ ዘዴዎች እያከናወነ መሆኑን ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ አስታወቀ
አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ሀብት ማገገሚያ ዘዴዎችን በመጠቀም (FMNR) በ2017 ዓ.ም ያከናወናቸውንና በ2018 ዕቅድ ላይ ድርጅቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቦንጋ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
ፕሮጀክቱ እንደ ሀገር በአምስት ዓመታት ዉስጥ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዱ መሬቶችን ለማገገም የሚያስችል አርሶ አደር መር የተፈጥሮ ሀብት ማገገሚያ ስልቶች እንዲተገበሩ እየሰራ መሆኑን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አለሙ ዳካ ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ የድጋፍና የክትትል ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል አቶ አለሙ።
በክልሉ በ2017 ዓ.ም ከ34 ሺህ 680 ሄክታር በላይ የተጎዱ መሬቶች እንዲለሙ መደረጉን የገለጹት አስተባባሪው፤ የለሙትም ከሰዉና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ ማድረግ እንደሚጠበቅ አክለዋል።
ማህበረሰቡ በተፈጥሮ ሀብት ላይ ተፅዕኖ እንዲያደርስ ችግሮችን በአግባቡ በመለየትና መፍትሔ በመስጠት እንዲሁም ቀጣይነት ያለውን ሥራ በማከናወን የፕሮግራሙ ዓላማ እንዲሳካ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ አስተባባሪው አሳስበዋል።
የተፈጥሮ ሀብትን ጥቅም ማህበረተሰቡ አዉቆ እና አምኖ እንዲጠብቅ የማንቃት ስራ በፕሮግራሙ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ አለሙ፤ በፕሮጀክቱ ለታቀፉ ማህበራት ደግሞ የኑሮ ማሻሻያ ድጋፎች እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በዘንድሮ አመት በክልሉ 35 ሺህ 417 ሄክታር የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ ለማድረግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ አስተያየት የሰጡት የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትልና የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዉብሸት ዘነበ፤ የተፈጥሮ ሀብት ማገገሚያ ዘዴዎችን (FMNR) በፕሮግራሙ የታቀፉ አርሶ አደሮች ተግባራዊ እንዲያደርጉ የመደገፍ እና የማስተባበር ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ዓላማው ግቡን እንዲመታ ቅንጅታዊ አሰራሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ አካላት በሰጡት አስተያየት ፕሮግራሙ በኑሮ ማሻሻያና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዉ የፕሮግራሙ ዕቅድ እንዲሳካ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በክልሉ በሚገኙት በሁሉም ዞኖች ላይ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ዘጋቢ፡ ቸርነት አባተ – ከማሻ ጣቢያችን
More Stories
በሩብ ዓመቱ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለመጀመሪያ ዙር ያሰለጠናቸውን ምልምሎች እያስመረቀ ነው
የፍትህ አስተዳድር ስርዓቱ ብቃትንና ሥነ-ምግባርን መሰረት ያደረገ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፍትህ ቢሮ አሳሰበ