አሳሳቢው የወባ በሽታና የተቋሙ መፍረስ

አሳሳቢው የወባ በሽታና የተቋሙ መፍረስ

በደረሰ አስፋው

ባለፈው እትማችን ከቀድሞው የኢትዮጵያ የወባ ማጥፊያ ድርጅት መፍረስ ጋር በተያያዘ በዘርፉ የካበተ ልምድ ካላቸው እንግዳና ተዛማች የማህደር ክምችታችን ጋር ሰፊ ቆይታ ማድረጋችን የሚታወስ ነው። የወባ ማጥፊያ ድርጅት ወባን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በተደረገው ጥረት ውጤታማ ስራዎችን ስለማስመዝገቡ አንስተናል፡፡ ይሁን እንጂ ተቋሙ ለምን ፈረሰ? ስንል ደግሞ ከሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘን ቀርበናል፡፡

የብዙ ዓመታት የሐገረ መንግስት ግንባታ ታሪክ ያላት ሀገር ውስጥ እየኖርን ጠንካራ ተቋማትን አለመገንባታችን የሚያስቆጭ ነው። ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ከአንድ ምእተ ዓመታት በላይ እንደሆናቸው የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተቋማት ነፋስ በነፈሰ ቁጥር የሚንገዳገዱ፤ ስርዓት በተለወጠ ቁጥር የሚፈርሱ ሆነው በመገንባታቸው የሚጠበቅባቸውን ውጤት ማምጣት አልቻሉም፡፡

ስለሆነም በሀገራችን የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ከስር መሰረታቸው ለመንቀል ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ተቋማትን መገንባት ለነገ የማይባል የቤት ስራ ነው፡፡ በሀገራችን የተከሰቱ ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎች፣ ማህበራዊ ችግሮችና የኢኮኖሚ መዳከሞች ምክንያቶቹ በርካታ ቢሆኑም ዋናው መነሻ ግን የተቋማት ግንባታ ስራ ደካማ መሆን ነው፡፡

አቶ ዘለቀ ከበደ በደቡብ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የሚድያ ሞኒተሪንግና ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በታሪክ፣ የ2ኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በፕሮጀክት ማኔጅመንት ሰርተዋል። በተለያዩ የሙያ ዘርፎችም በማገልገል የካበተ ልምድ አላቸው፡፡ በኢትዮጵያ ተቋማት ብቅ ብለው መክሰማቸው ምክንያቱ ምንድነው? እንደሀገር የሚያስከትለው ተጽእኖስ እንዴት ይታያል? ለሀገር ጠቃሚ ሆነው ሳለ ባልታወቀ መልኩ መጥፋታቸው የውጭ ተጽእኖ ይኖረው ይሆን? ስንል ከጥያቄ በመነሳት ነው ውይይታችንን የጀመርነው፡፡

የተቋማት ግንባታ በኢትዮጵያ ውስንነት ያለበት ሂደት መሆኑ በጥናት መመላከቱን አቶ ዘለቀ ጠቅሰዋል፡፡ ወጥነት ያለው እድገት ያለመኖር፤ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እና ተጠያቂነት አለመኖር እንዲሁም ለተቋማት በቂ የሆኑ ግብዓቶች አለመሟላታቸውም እንደችግር ይጠቀሳል፡፡ ተቋማት ውጤታማ ሆነው እንዲቀጥሉ አልያም እንዲከስሙ አስተዋጽኦ የሚያደርገው የሀገራት ፖሊሲ ነው ሲሉም ያክላሉ፡፡ የአንድ ሀገር ፖሊሲ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን፣ የህብረተሰቡ የኑሮ ሁኔታ፣ ያለፉ ታሪኮችንም መለስ ብሎ መቃኘትና በጥናት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል፡፡

ያደጉ ሀገራት አንድ ጊዜ ፖሊሲና ስትራቴጂያቸውን ይዘረጋሉ እንጂ ተቋማትን የማጥፋት ልማድ የላቸውም፡፡ ውጫዊና ውስጣዊ መሰረቶችን አድርገው ስለሚሰሩ። መነሻቸውና መሰረታቸው የጸና ነው። የእኛን ሀገር የፖሊሲና የተቋማት ግንባታን ስንመለከት ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው ይላሉ፡፡ የሚወጡ ፖሊሲዎች የችኮላ እና ብዙ ነገር የሚጎላቸው በመሆኑ ስርዓት ሲለወጥ አብረው ይጠፋሉ።

ፖሊሲዎቻችን የፖለቲካ ፍላጎቶችን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውንም በችግርነት ያነሳሉ፡፡ ተቋማትን የምናቆይበት እውቀት፣ ልምድና ፍላጎት አናሳ በመሆኑ ተቋማት ብቅ ይሉና መልሰው ሲፈርሱ ይታያሉ ብለዋል። ሀገርን የሚያሻግሩ ጠቃሚ ፖሊሲዎች መንግስታት ሲለዋወጡ ደብዛቸው ይጠፋሉ። በተቃራኒው ደግሞ ጥቅም የሌላቸውም ሲመሰረቱ ይስተዋላል። በዚህም ሀገር እየተጎዳች ስለመሆኑ ነው አቶ ዘለቀ ያብራሩት፡፡ ደርግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ኃይለስላሴን ስለጠላ የሀገር ባለውለታ የሆኑ ተቋማት ሲጠፉ ተመልክተናል፡፡

በተለይ ይላሉ አቶ ዘለቀ ፖሊሲዎቻችን የሚወጡት የውጭውን ዓለም ድጋፍ ያገኛል በሚል መሆኑ ለችግር አጋልጦናል ባይ ናቸው። ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት ጠቃሚ ሆነው ሳለ እንዲጠፉ ከተደረጉት ተቋማት ውስጥ የቀድሞ የኢትዮጵያ የወባ ማጥፊያ ድርጅትን ለአብነት ይጠቅሳሉ። በሀገራችን ብሎም በአፍሪካ ግንባር ቀደም የሆነ የወባ ማጥፊያ ድርጅት እንደነበርም ያነሳሉ፡፡ “ተቋሙ ውጤታማ እንደነበር እኛው ምስክር ነን” ያሉት አቶ ዘለቀ ውጤታማ ከሆነ ለምን እንዲጠፋ ተደረገ? የሚለው እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ጠቅሰዋል። “ውጤታማ ከሆነስ አሁን መልሶ ማቋቋም ለምን አልተቻለም?” ሲሉም ይጠይቃሉ። በስልጣን ላይ ያሉ አካላት የኋላ ታሪክን መለስ ብሎ አለማየት አለዚያም የውጭ እርዳታ ሰጪዎችም የራሳቸው ዓላማ ማስፈጸሚያ ሆኖ ካልተገኘ እንዲጠፋ እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት፡፡

በውጭ ጥገኝነት ላይ የተመሰረተ የተቋም ግንባታ ደግሞ ሀገርን የሚያሻግር አይደለምና ሊታረም ይገባል ይላሉ፡፡ በተመሳሳይ የፖለቲካ ባህላችንም ለተቋማት ውድቀት ምክንያት እንደሆነም ያነሳሉ፡፡ የተቋማት ግንባታ መነሻ የሚያደርገው የፖለቲከኞችን ፍላጎት እንጂ ከሀገር ጥቅም ጋር የተሳሰረ አለመሆኑን በመጠቆም፡፡ ሹመኞች እራሳቸውን በስልጣን ሊያቆያቸው በሚችሉ አደረጃጀቶች ላይ ነው ትኩረታቸው ሲሉ የገለጹ ሲሆን ይህም አንዳንዴ ታይተው ድርግም ለሚሉ ተቋማት ምክንያት ናቸው ብለዋል፡፡

የመንግስትና የፓርቲ ስራ መደበላለቅም ሌላው ለተቋማት መፍረስ ምክንያት እንደሆነ በማሳያነት ያቀርባሉ፡፡ ፖሊሲ የሚቀርጹ ሰዎች የፓርቲ ሰዎች ናቸው፡፡ አሁን ያሉት የተቋማት መሪዎችን ብንመለከት የዚሁ ሰለባ ናቸው፡፡ የዕውቀቱ ባለቤቶች ሀሳብ ሲያቀርቡ እንደ ሀገር አፍራሽነት የሚፈረጁበት ጊዜም ታይቷል፡፡ በዚህም ጠቃሚ ተቋማትን ማዝለቅ አይደለም ተቋም መፍጠር አልተቻለም ነው ያሉት፡፡

ለጋሾች ለዲሞክራሲ ግንባታ፣ የሰብአዊ ድጋፍ፣ የማህበራዊ ተቋማት ድጋፍ በሚል እጃቸውን ያስገቡና መልሰው ድጋፋቸውን ያቆማሉ፤ ተቋማትም እንዲጠፉ ይገደዳሉ፡፡ የወባ ማጥፊያ ድርጅት የመጥፋቱ ምክንያት ይሄው ነው ሲሉ ነው የገለጹት፡፡ ሀገር በቀል የሆኑ አስተሳሰቦች፣ ዕውቀቶች፣ ባህሎች በሀገር ውስጥ እንዳይሰርጽ በማድረግ የእነሱ ጥገኛ ሆነን እንድንዘልቅ ነው ምኞታቸው። ጠቃሚ ተቋማት እንዳይፈጠሩ ከተፈጠሩም እንዲጠፉ ያደርጋሉ፡፡ በውጭ ድጋፍ የሚቋቋሙ ተቋማት መጨረሻቸው መጥፋት ነው፡፡ ከእነሱ ተጽእኖ አሻፈረኝ የሚሉ ካሉም ያጠፏቸዋል ብለዋል፡፡

የተቋም ግንባታ ስንል መንግስታት በተለዋወጡ ቁጥር የማይናወጥ፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ እና ከተጽእኖ ነጻ የሆኑ ተቋማትን የመገንባት ሒደት ነው፡፡ ሀገራችን ለዘመናት በማያቋርጥ ቀውስና ማባሪያ በሌላቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች ውስጥ እንድትገባ የሆነችው የተቋም ግንባታ ላይ ዘላቂ የሆነ ስራ ባለመሰራቱ ነው፡፡

ስለሆነም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በጠንካራ ዓለት ላይ የተገነባ ተቋም እንዳይፈጠር ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በመንቀስ ለችግሮቹ መፍትሔ ማበጀት ይገባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የወባ መቆጣጠሪያ ባለሙያዎች ማህበር የተቋማት መፍረስን ከሚቃወሙ የሙያ ማህበራት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ዘኪዎስ ገቲሶ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የወባ ማጥፊያ ድርጅት ውስጥ በተለያዩ ሙያ ዘርፎች ስልጠና ወስደው ሀገርንና ህዝብን ሲያገለግሉ በነበሩ ባለሙያዎች በ1995 ዓ.ም የተቋቋመ ማህበር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የማህበሩ አባላት በጡረታ ከሚወዱት ስራቸው ቢሰናበቱም አሁንም የክልሉን የባለሙያ ክፍተት ለመሙላት ማህበሩን እንደመሰረቱ ነው የተናገሩት፡፡ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ሀገር አቀፍ እንቅስቃሴ በአጋርነት በመሰለፍ ስልጠና እና የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት የወባ በሽታ የህብረተሰቡ የጤና፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግር እንዳይሆን በሙያቸው አስተዋጽኦ ለማበርከት በሚል የተቋቋመ የሙያ ማህበር እንደሆነም ገልጸውልናል፡፡

አቶ ዘኪዎስ የቀድሞው የወባ ማጥፊያ ድርጅት በሀገር ውስጥና በውጭ ስልጠናውን ወስደው የበቁ በሺህ የሚቆጠሩ ባለሙያዎች አፍርቶ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ተቋሙ የተጠናከረ የመዋቅር፣ የአስተዳደር፣ የቴክኒክ አገልግሎት በመዘርጋትና በአገልግሎቱ መልካም የስራ ውጤትም አስገኝቶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ በሰጠው አገልግሎት ከ30 እስከ 40 በመቶ የነበሩ የወባ አካባቢዎችን ወደ 5 በመቶ እና ከዚያ በታች ዝቅ ብሎ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ፕሮግራሙ በመላው ሀገሪቱ እስከ 1980 ዓ.ም እንዲዳረስ ታስቦ ሲሰራ ቢቆይም ይህ ተግባራዊ ሳይሆን ፕሮግራሙ ተቋረጠ ወይም ድርጅቱ ፈረሰ ይላሉ፡፡ ይህንን ተግባርም በመኮነን፡፡

የወባ ማጥፊያ ድርጅት ላይ የተደረጉ መዋቅራዊ ለውጦች ያስከተላቸው ችግሮች መኖራቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ውህደት ተብሎ የተፈጸመው ተቋምን የማፍረስ አካሄድ ችግር ያለበት እንደሆነም አንስተዋል።

“ወባ ቀንሷል፤ መቆጣጠር እንችላለን” በሚል የተደረገው ችኩል ስራ ዛሬ ላይ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል፡፡

“ወባን ማጥፋት” ከሚለው ወደ “ወባን መቆጣጠር” በሚል መቀየሩ በራሱ ችግር ያለበት እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ ጠቃሚ ተቋማትን ማጠናከር ሲገባ ማፍረሱ ተገቢ አለመሆኑን በመጠቆም።

በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ተመርቆ ስራ የጀመረው ተቋም ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ በሆኑ ወባ መቆጣጠር ስራዎች ውጤታማ ተቋም እንደነበር ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስታውሳሉ አቶ ዘኪዎስ፡፡ የበጀት ድጋፍ የሚያደርጉ የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅትና የዓለም የጤና ድርጅት እጃቸውን መሰብሰባቸውም በቀጥታ ባይሆንም ሌላ እንድምታ ሊኖረው ይችላል የሚል ጥርጣሬም አላቸው፡፡ ከዚህ ደግሞ ልንማርና ሀገር በቀል ተቋማትን ልንመሰርት ይገባል ባይ ናቸው፡፡

አሁን ላይ ብሄራዊ የወባና ሌሎች ቬክተር ወለድ በሽታዎች ተብሎ ከሌሎች በሽታዎች ጋር ተለጥፎ ያመጣው ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን አንስተዋል፡፡ ይልቁንስ ከአቅሙ በላይ ተለጥጦ በመዋቀሩ ወባን ለመከላከልም ሆነ ለመቆጣጠር ያስቻለ ሆኖ እንዳላዩት ነው ትዝብታቸውን ያጋሩን፡፡ ወባ በየጊዜው እያገረሸ ችግር የሚፈጥረውም ከዚህ ስህተት የመነጨ እንደሆነ ነው ልምዳቸውን ያጋሩን፡፡

ከሁሉም በላይ በጤና ድርጅት የሚገኙ ባለሙያዎች ስለወባ በሽታ መሰረታዊ ግንዛቤ እንዳላቸው የማይካድ ቢሆንም ስለትንኝ ጥናት እና ስለሌሎችም የወባ በሽታ የመስክ የስራ እንቅስቃሴዎች ስልጠና ሳይሰጥ ኃላፊነት እንዲሸከሙ መደረጉ የስራ ጫና ከመፍጠር በዘለለ ያመጣው ፋይዳ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በኢትዮጵያ ከንጉሱ እስከ ደርግ መውደቅ ድረስ ባሉት ተከታታይ ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች ጥሩ የሚባል ውጤት ተመዝግቦ ነበር፡፡ ወባ በወረርሽኝ መልክ እየተከሰተ የሚያሳድረው ጫና የመቀነስ አዝማሚያ ታይቶበትም ነበር፡፡ አንዳንድ አካባቢዎችም የመጥፋት አዝማሚያዎች እንደነበሩ በማስታወስ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ከደርግ መውደቅ በኋላ ግን ተቋሙ ፈረሰ፤ ባለሙያዎችም ተበተኑ፡፡ የሞት ምጣኔውም በየጊዜው በወረርሽኝ መልክ እየተከሰተ የሀገር ስጋት እንደሆነ ቀጥሏል ብለዋል፡፡

ስለዚህ የቀድሞውን የወባ ማጥፊያ ድርጅት መልሶ ማምጣት አዳጋች ቢሆንም የተሻለ አሰራርን በመዘርጋት ወባን ከሀገራችን ለማጥፋት ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። ጊዜውም ፈጠራንና ሀብትን ሥራ ላይ በማዋል ወባን የምናስወግድበት ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የማህበሩ ሊቀመንበር ይህን ይበሉ እንጂ በቀድሞው የኢትዮጵያ ወባ ማጥፊያ ድርጅት ውስጥ በደም ጥናት ቴክኒሺያንነት ያገለገሉት አቶ ግርማ ገብራይ የሰጡን አስተያየት ከዚህ በተቃራኒው ስለመሆኑ ነው፡፡ ማህበሩ ለስም ተመሰረተ እንጂ መንግስትን በመሞገት ከወባ ጋር በተያያዘ መሠራት የሚገባውን ያህል አልሰራም፡፡

የወባ ጉዳይ የሃገሪቱ አንገብጋቢ ችግር በመሆኑ የማህበሩ አባላት ያላቸውን የካበተ እውቀትና ልምድ ለሃገር ጥቅም ማዋል ሲገባቸው ይህ ባለመሆኑ እንደሚቆጩም ነው የተናገሩት፡፡

“ማወቅ በሽታ ነው” እንዳሉት እሳቸውም እውቀታቸውን ለዚህ በጐ አላማ አለማዋል ተገቢ አለመሆኑን ነው፡፡ እኛም የወባ ጉዳይ የሃገሪቷ የጤና፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ከመሆኑ ጋር የሃገሪቷ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት ለምን ተቸገሩ? ስንል ፅሑፋችንን ቋጨን፡፡