“ቅን ልብ ያለው ሁሉ ወገኑን ከጭንቀት ማሳረፍ ይችላል”

“ቅን ልብ ያለው ሁሉ ወገኑን ከጭንቀት ማሳረፍ ይችላል”

በአለምሸት ግርማ

ከመልካም እሴቶቻችን መካከል መረዳዳት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ይህም አንዱ በሌላው ውስጥ ትልቅ ዋጋ እንዲኖረው ያደርጋል ሰዋዊ ተግባር ሲሆን አንዱ ለሌላው አስፈላጊ በመሆኑ የሰዎችን የእርስ በእርስ ግንኙነትንም በእጅጉ ያጠናክራል።

የዛሬው ባለታሪካችን የሃዋሳ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ሰዎችን ለመርዳት የሚጓጓ ቅን ልብ ያላቸው ሰው መሆናቸውን የቅርብ ጓደኞቻቸው ይመሰክራሉ። የተለያዩ በጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ይሳተፋሉ። “ነገር ግን ለሚዲያ የሚቀርብ ተግባር የለኝም፤ ገና ምን ሰራሁና” ብለውን ነበር።

አቶ አለማየሁ ሙሉጌታ ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት ሃዋሳ ከተማ አዲስ አበባ ሰፈር ነው። ከቤተሰቦቻቸው ከተማሩት መልካም ነገር አንዱ የተቸገረ ሰውን መርዳት መሆኑን በአፅንኦት ይናገራሉ።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት ታቦር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም ታቦር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ውጤት ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ በቂ አልሆነላቸውም። ይሁን እንጂ ልጅ እያሉ የጀመሩትን የዶሮ ማርባት ስራ አጠናክረው ቀጠሉ። ሌሎች የንግድ ስራዎችንም ጎን ለጎን ያከናውኑ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አፍሪካ ቤዛ የሚባል የግል ኮሌጅ በመግባት በአካውንቲንግ የትምህርት ዘርፍ በዲፕሎማ መርሃ-ግብር ተመረቁ።

በወቅቱ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሂሳብ ሰራተኛ ማስታወቂያ አውጥቶ ስለነበር ተወዳድረው የመቀጠር ዕድሉን አገኙ። በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሂሳብ ሰራተኛነት እያገለገሉ የማታ ትምህርት በቢዝነስ ማናጅመንት በመከታተል በዲግሪ መርሃ-ግብር ተመረቁ። ጎን ለጎን የንግድ ስራውንም አላቆሙም ነበር።

በመቀጠልም በህንድ ሀገር ከሚገኝ ‘ኢንትራጋንዲ’ ከሚባል ዩኒቨርሲቲ 2ኛ ዲግሪያቸውን አገኙ። በዚህ ሂደት ውስጥ እያሉ ነው ሰውን ወደ መርዳት ስራ የገቡት።

አቶ አለማየሁ “ሰውን ለመርዳት ሀብታም መሆን አያስፈልግም” የሚል እምነት አላቸው። ለዚህ አስተሳሰብ ያበቁት ደግሞ ቤተሰቦቹ እንደሆኑም ይናገራሉ። ቤተሰቦቻቸው ሰውን በመርዳት ያምናሉ። ይወዳሉ። “ያንን ተግባር እያየሁ ማደጌ ቀስ በቀስ ወደዚህ ተግባር እንድገባ አድርጎኛል” ይላሉ።

ሃዋሳ ታቦር ትምህርት ቤትን ከ40 አመታት በላይ በጥበቃ ያገለገሉት አቶ ዮሴፍ የሚባሉ ግለሰብ ቤተሰብን ችግር በመመልከታቸው የቤተሰቡን ቤት ማደስ ችለዋል። ቤተሰቡንና ጓደኞቻቸውን አስተባብረው ለቤቱ እድሳት ካደረጉ በኋላ ለልጃቸው በየወሩ የ2ሺ ብር ተቆራጭ እያደረጉ ይገኛሉ።

በተግባሩ ቤተሰቦቻቸው ደስተኞች መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ አለማየሁ በተለይም አሜሪካን ሀገር የምትገኘው እህታቸው ሰውን የመርዳት ከፍተኛ ፍቅር እንዳላት ይናገራሉ። በሚያከናውኗቸው ሰዎችን የመደገፍ ስራዎች በሃሳቧም ሆነ ባላት አቅም ታግዛቸዋለች። በዘንድሮው የገና በዓል ዋዜማ ለአባታቸው የሙት ዓመት መታሰቢያ ያዘጋጁትን በሬ በማረድ ከሽንኩርት እና ዘይት ጋር ለ24 አቅመ ደካሞች እንዲካፈል ያደረጉ ሲሆን ይህም ተግባር በየአመቱ የሚቀጥል ነው ብለዋል። ድጋፍ ለሚሹ ህፃናትም አልባሳትን አበርክተዋል። “ለአቅመ ደካሞች ምግብን አብስሎ ከመመገብ ይልቅ ወደ ቤታቸው እንዲወስዱት ማድረግ በተቀባዮች ላይ ደስታውን ይጨምረዋል። ሌሎችም ከዚህ ሊማሩ ይገባል” ይላሉ። በሚደገፉት ሰዎች ዘንድ የሚታየው የደስታ ስሜት እርካታን እንደሚፈጥርላቸው ይናገራሉ፡-

“ካለን ላይ ሌሎችን መርዳት መልመድ ተገቢ ነው። ሁለት ወይም ከዛ በላይ ያለንን ነገር አንዱን ምንም ለሌለው ማካፈል ያስፈልጋል። ገንዘብ ደስታ አይሰጥም። ገንዘባችንን መልካም ነገር ስንሰራበት ግን ሃሴትን ይፈጥርልናል።

ሰውን መደገፍ በውስጤ የነበረ ሃሳብ ነው። አሁን ዕድሉን አግኝቼ እያደረኩት ቢሆንም በእኔ እይታ ግን ጅምር ላይ ነው እንጂ በቂ አይደለም። በመሆኑም ወደ ፊት የምሰራቸው በዕቅድ ደረጃ ያሉ ሃሳቦች አሉኝ። ከ5 ወይም ከ6 ዓመታት በኋላ ተግባራዊ የሚሆን ዕቅድ በእጄ ላይ አለ። ያንን ተግባራዊ ለማድረግ የዝግጅት ስራዎችን እየሰራሁ እገኛለሁ።”

“ስንተባበር ሁሉ ነገር ይቀላል። ብንረዳዳ ድህነትን ማስወገድ እንችላለን። ለመረዳዳት ደግሞ ባለሀብት መሆን አይጠበቅብንም። ካለን ማካፈል እንዲሁም መስራት እና መለወጥ ለሚፈልግ ደግሞ በመተባበር ስራ ማስጀመር ይቻላል። ዛሬ የደገፍነው ሰው ነገ ሲለወጥ ችግርን ስለሚያውቀው ሌሎችን ለመርዳት ቀስቃሽ አያስፈልገውም” ይላሉ።

በመረዳዳት ጎዳና የሚወጡ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ እንችላለን። ነገር ግን የራሳችንን ምቾት ብቻ የምናይ ከሆነ የሰው ልጅ ፍላጎት ማለቂያ ስለሌለው ለሌሎች የሚሆን ጊዜም ገንዘብም አይኖረንም። ስለዚህ ቢያንስ በቀን አንዴ መብላት የማይችሉ ሰዎች መኖራቸውን እያሰብን ካለን በመቀነስ እና በማካፈል የውስጥ ደስታን እናገኛለን።

“በአንድ ወቅት ዝዋይ ደሴት ላይ የሚኖሩ አንዲት እናት በ‘ኢቢኤስ’ ሚዲያ ቀርበው ከተመለከትኩ በኋላ ቢያንስ በየ3 ወሩ እየሄድኩ እጠይቃቸዋለሁ። ባለኝ አቅምም አደግፋቸዋለሁ። የወደ ፊት ዕቅዴ ሲሳካ እሳቸውን ጨምሮ እንደእሳቸው ያሉ እናቶችን በሰፊው የመንከባከብ ስራ የመስራት ዕቅድም አለኝ።”

ከዚህ በተጓዳኝ በዶሬ ወረዳ ሳማ ኤጀርሳ ቀበሌ 60 ተማሪዎችን እንደሚያስተምሩም በቅርበት የሚያውቋቸው ሰዎች አጫውተውናል። ስለስራው አጀማመር ጠይቀናቸው እንዲህ በማለት አስረድተውናል፦

“በአካባቢው ዘመድ ጥየቃ የመሔድ ዕድል አለኝ። በዚያ ቀበሌ ሳልፍ ልጆች በትምህርት ሰዓት ሲጫወቱ አያለሁ። ሰዎችን ስጠይቅ ትምህርት ቤቱ ካሉበት ቀበሌ 5ኪሎ ሜትር ርቀት ስላለው ልጆች የመማር ዕድል አጥተዋል። ይህንን ጉዳይ በተደጋጋሚ ስመለከት አንድ ሃሳብ ወደ ልቤ መጣ። ለቤተሰቦቼም አማከርኳቸው። በሃሳቡ ተስማማን። በዚያ ሃሳብ መነሻነት በአካባቢው ያሉ ትምህርት ቤት ያልገቡ ታዳጊዎችን ሰብስበን፤ አስተማሪ ቀጥረን የቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲማሩ የማድረግ ስራ ተጀመረ። ስራውን ለማጠናከር ብስኩት እየሰጠን ተማሪዎችን መሳብ ጀመርን። በዚያም 60 ልጆችን የቅድመ መደበኛ ትምህርት እየተማሩ ሲሆን ስራው ከተጀመረ አሁን ሶስት ዓመት ሆኖታል።”

5 ኪሎ ሜትር ተጉዘው በመማራቸው ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የማቋረጥ ሁኔታ የነበረ ሲሆን አሁን ግን እየተሻሻለ መምጣቱን ይናገራሉ። በተለይም ልጆች ትምህርት ቤት ከመግቢያ ዕድሜያቸው ዘግይተው ስለሚገቡ የትምህርት ፍላጎታቸው ላይ ጫና የነበረባቸው ሲሆን አሁን ግን ችግሩ እየቀነሰ መምጣቱን አጫውተውናል።

በቀጣይም ትምህርት ቤቱን ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለማሳደግ በስራ ላይ ይገኛሉ። በቀበሌው ከ3መቶ በላይ አባወራዎች የሚኖሩ ሲሆን ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ችግር እንዳለበትም አጫውተውናል። በአካባቢው በስፋት የሚመረተው በቆሎ ነው። ስለዚህ የአካባቢውን ህብረተሰብ ጫና ለመቀነስ እንዲቻል ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነግረውናል። ይህንን ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ ከቤተሰብና ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተጀመረ ስራ መኖሩንም ጨምረው ገልፀዋል።

በተለይም በክረምት ጊዜ መንገዱ አስቸጋሪ ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ቀይ አፈር የመድፋት ስራ አልፎ አልፎ እንሰራለን። ይህም በተለይ ለወሊድ የቀረቡ እናቶች ፈጥነው ወደ ጤና ተቋም እንዲደርሱ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

አቶ አለማየሁ ስለመረዳዳት እንዲህ ይላሉ፦ “ሰዎችን የምንረዳው በዓላት ሲመጡ ወይም ወቅት ጠብቀን ብቻ መሆን የለበትም። ሁሌም የሰውን እገዛ የሚፈልጉ አቅመ ደካሞች እንዲሁም ህክምና የሚፈልጉ አሉ። የዕለት ጉርስ ማግኘት የማይችሉ ብዙዎች ናቸው። ስለዚህ እነዚህ ወገኖች ለበዓል እንዲደርሱ ዛሬን ልንመግባቸው እና ልናግዛቸው ይገባል። ካለን ማካፈል የዘወትር ተግባራችን እና ባህላችን ቢሆን መልካም ነው።

“ሁሉን ነገር ከመንግስት መጠበቅ አያስፈልግም። እኛም እንደዜጋ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል። መንግስት መድረስ ያልቻለባቸውን አካባቢዎች መልካም ፈቃድ ያለን ሰዎች ብንደርስ ጥሩ ነው። ስንተባበር የወገናችንን ችግር መቅረፍ ቀላል ይሆናል። መረዳዳት ሲታሰብ ሁል ጊዜ ከውጭ ሀገራት መጠበቅ ተገቢ አይደለም። ቅን ልብ ያለው ሁሉ ወገኑን ከጭንቀት ማሳረፍ እና መርዳት ይችላል።”

አቶ አለማየሁ ጊዜው ሲደርስ ሙሉ ጊዜያቸውን ለበጎ ተግባር የማዋል ትልቅ ዕቅድ አላቸው። እናታቸውን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸው የበጎ ተግባር ሃሳባቸውን እንደሚደግፉም አጫውተውናል። እኛም የልባቸው እንዲሰምር ተመኘን!