በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጌዴኦ ዞን በ2017 ዓ.ም በመኸር እርሻ ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን አቅዶ እየሠራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ
በመኸር እርሻ ወቅት ከሚለሙ የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችም ከአንድ ሚሊዮን 6 መቶ ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ መምሪያው ገልጿል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በድሉ አየለ፤ ለመኸር እርሻ ዝግጅት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ በስፋት ተወያይተውና ንቅናቄ በመፍጠር ወደ ትግባራ መግባታቸውን አስረድተዋል።
ከተረጂነት በመላቀቅ ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በሚደረገው ጥረት ላይ ከሴፍቲኔት ተመርቀው የወጡ ሰዎችም ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ወደ እርሻ ሥራ በማስገባትና ሌሎችን በማስተባበር ምንም ዓይነት መሬት በዞኑ ጾም እንዳያድር ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
በዞኑ በቡሌ፣ ራጴ እና ጮርሶ ወረዳዎች ላይ በአሲዳማነት ተጠቅተወ ምርታማነት ላይ ተፅዕኖ ሲያሳድሩ የነበሩ መሬቶችን ከአሥራ አምስት ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ ተጠቅመው ማከማቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ ይህም ምርታማነት ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።
በበልግ ወቅት ከዕቅድ በላይ በመሸፈን ከሚጠበቀው ምርት በላይ እንዲገኝ አስችሏል ያሉት አቶ በድሉ፤ በበልግ እርሻ የነበሩ ጠንካራ ተግባራትን በማበረታታት ክፍተት የታየባቸውን ደግሞ በማረም ለመኸር እርሻ በትኩረት እንዲሠራ የድጋፍና ክትትል ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ በእርሻ ዘርፍ የአዝርዕት ልማት አስተባባሪ አቶ ዘነበ ከበደ፤ ለመኸር እርሻ ከ24 ሺህ 3 መቶ 30 ሄክታር ማሳ ለመሸፈን አቅደው የእርሻ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም 1 ሚሊዮን 6 መቶ 76 ሺህ 1 መቶ 54 ኩንታል ምርት ከተለያዩ አትክልቶች፣ ፍራፍሬዎች እና ሰብሎች እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።
ለመኸር እርሻ ዝግጅት 6 ሺህ 4 መቶ 91 ኩንታል ዳፕ፣ 4 ሺህ 15 ኩንታል ዩሪያ እና 34 ሺህ 7 መቶ 47 ኩንታል የተለያዩ የሰብል ዘሮች ያሰፈልጋል ያሉት አስተባባሪው፤ ከዋጋ መጨመር ውጪ የግብኣት አቅርቦት እጥረት አለመኖሩን ተናግረዋል።
በዞኑ ባለው በተበጣጠሰ መሬት ላይ መካናይዜሽንና ቴከኖሎጂን ለመጠቀም ያስቸግራል ያሉት አቶ ዘነበ፤ በኩታ ገጠም ማምረት ለሁሉም ነገር አመቺ በመሆኑ ከ8 ሺህ 4 መቶ ሄክታር መሬት በላይ በዞኑ በኩታ ገጠም እርሻ እንዲለማ ታቅዶ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡ ተስፋዬ ጎበና – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጌዴኦ ዞን በ2017 ዓ.ም በመኸር እርሻ ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን አቅዶ እየሠራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ

More Stories
በተቋማትና በባለሙያዎች መካከል የውድድር መንፈስ በመፍጠር ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ
”የምንተክላቸው ችግኞች ለትውልድ ተሻጋሪ ትሩፋትን የሚያስገኙ ናቸው” – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ
ከማረምና ማነጽ ጎን ለጎን የሀገሪቱን አረንጓዴ ልማት እስትራቴጂን ለማሳካት ሚናውን እንደሚወጣ የጂንካ ማረሚያ ተቋም አስታወቀ