በዞኑ በበልግና በመኸር ወቅት የተከናወኑ የግብርና ስራዎች የተሻለ ውጤት መታየቱን የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለጹ
በዞኑ እኖር ወረዳ የገረንቦ ቀበሌ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በወረዳው አስፈላጊውን ግብአት እና የባለሙያ ድጋፍ በማግኘታቸው ከአምናው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጪ ጋሩማ በዞኑ በበልግና በመኸር ወቅት የተከናወኑ የግብርና ስራዎች የተሻለ ውጤት የታየባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
አርሶአደሮቹ የኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን መጠቀማቸው የበለጠ ወጤታማ እንደሚደርጋቸው ነው ዋና አስተዳዳሪው ያስረዱት።
በባለሙያ ምክረ ሃሳብ በመታገዝ እየሰሩ መሆናቸው የሰብሎቹ አሁን ያሉበት ቁመና ማሳያ ነው ያሉት አቶ ላጫ፤ ይህንንም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዞኑ በአበሽጌ፣ ቸሃ፣ እዣ እና እኖር ወረዳዎች ሰፋፊ መሬቶች በበቆሎ፣ በጤፍ፣ ስንዴና ገብስ ሰብሎች በኩታ ገጠም በበልግና በመኸር እየተሸፈኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በተለይም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በማከናወን በጠረጴዛማ እርከን ላይ የተሰሩ የገብስና የስንዴ ማሳዎች በሃገር አቀፍ ደረጃ ተሞክሮ ሊወሰድባቸው የሚችሉ ተግባራት ናቸው ሲሉም አቶ ላጫ ጋሩማ አብራርተዋል።
ግብርና ከድህነት መውጫ ዋነኛው መንገድ ነው የሚሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ አርሶአደሩ በዚህ ዘርፍ የተቀናጀ ስራ ከሰራ የምግብ ዋስትናውን የሚያረጋግጥበት በመሆኑ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታልም ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የማይታረሱ የወል መሬቶች ስራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት በመስኖ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በበልግና በመኸር ተግባራት ላይ እንዲሳተፉና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አውስተዋል።
የእኖር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቱ ተክሌ በበኩላቸው፤ በወረዳው በበልግ ወቅት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ በርካታ ተግባራት መከናወኑን ገልጸዋል።
በዚህም ከ2 ሺ 5 መቶ ሄክታር መሬት በላይ በበቆሎ በሜካናይዜሽን መሸፈኑንና አፈጻጸሙ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር 8 መቶ ሄክታር መሬት ጭማሪ ያለው መሆኑንም አቶ መብራቱ ተናግረዋል።
በመኸር ወቅት አንድም መሬት ጾሙን ማደር የለበትም በሚል እሳቤ ንቅናቄ በመፍጠር ከ11 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በዘር መሸፈኑን ገልፀዋል።
እንደሃገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ወረዳው የራሱን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝም ሃላፊው አመላክተዋል።
በወረዳው የገረንቦ ቀበሌ አርሶደሮች በሰጡት አስተያየት አስፈላጊውን ግበአት እና የባለሙያ ድጋፍ በማግኘታቸው ከአምናው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
በተለይም በአምናው የመኸር ወቅት የነበሩ ክፍተቶችን በመቅረፍ እና ተሞክሮ በመውሰድ እንዲሁም ልዩ ትኩረት በመስጠት የግብርና ስራዎቻቸውን እያከናወኑ እንደሚገኙም አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡ አስቻለው አማረ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
“ባለፉት ሰባት ዓመታት የክልሉ ገቢ የመሠብሰብ አቅም ከ7 ቢሊዮን ብር ወደ 13 ቢሊዮን ብር አድጓል” – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
የግብርና ዘርፍ የእሴት ሰንሰለትን በመከተል የስራ ዕድልን መፍጠር በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ገለፀ
በጥረቱ ውጤታማ የሆነው ወጣት ተሞክሮ!