ቦርሳ ጠፋብኝ! አዲስ ሥራ¡

ቦርሳ ጠፋብኝ! አዲስ ሥራ¡

በአለምሸት ግርማ

በተፃፈላቸው የሚኖሩ ብቸኛ ፍጠረታት ይመስሉኛል። በነፋሻማው አየር ላይ የሚበሩት አዕዋፋት። እኛ አለን እንጂ አታድርጉ የተባልነውን እያደረግን፤ አድርጉ የተባልነውን ማድረግ ተቸግረን ስንዳክር ከዕጣ ፋንታችን ጋር ሳንገናኝ ዕድሜያችንን የምናጠናቅቅ።

ይህን የማሰላስለው ከሃዋሳ ወደ ሶዶ ከተማ በመጓዝ ላይ እያለሁ ነበር። አየሩ ቀዝቀዝ ያለ፥ ዝናቡም ለመዝነብ እየተሰናዳ ባለበት ጊዜ ነው። በመስኮት በኩል ግራና ቀኙን እያየሁ ነበር የምጓዘው። መስመራችን በዲምቱ በኩል ነው። የግራ ቀኙ ልምላሜ ይማርካል። በቆሎ፣ ድንች፣ እንሰት መሬቱን በአረንጓዴ ከሸፈኑት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

ከተሞቹን አለፍ ስንል በገጠራማው አካባቢ ካሉ የሳር ቤቶች የሚወጣው ጢስ ብርዱን ለመከላከል ትግሎች እየተደረጉ ስለመሆኑ ይናገራል። ጢሱ ምናልባት በከተማ ለሚኖር ሰው ትርጉም ባይኖረውም በውስጡ ላሉት ግን ብዙ ነገራቸው ነው። ደሳሳ በምትመስለው ጎጆ ውስጥ ቤተሰባዊ ፍቅርን፣ ጨዋታን፣ ደስታን … ብቻ ብዙ ነገር ይካፈሉበታል።

ከሃሳቤ መለስ ስል መኪና ውስጥ ያለው የተሳፋሪው ጭውውትም ድካም እንዳይሰማ ያደርጋል። የህዝብ ትራንስፖርት ከሚሰጠው ዋነኛ ጠቀሜታ ባሻገር ሰዎች እንዲተዋወቁ ሃሳብ እንዲቀያየሩ ዕድል ይፈጥራል። ከጊዜያዊ ጭውውት አለፍ ሲልም ለተለያዩ ቁምነገሮች ሰዎች የሚገናኙበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል።

በዚህ ሁኔታ ጉዟችንን እያገባደድን ባለንበት ወቅት መኪናው አንድ ስፍራ ላይ ቆመ። አየር ተቀበሉ አለ- ረዳቱ። አብዛኛው ሰው ከመኪናው ወረደ። ከደቂቃዎች ቆይታ በኋላ የወረዱት ሰዎች ወደ መኪናው በመመለስ በቦታቸው ላይ ተቀመጡ። በዚህ መካከል ነበር አዲስ ነገር የተሰማው።

አንዲት መንገደኛ “ወይኔ ቦርሳዬ! ወይኔ ብሬ!” እያለች መጮህ ጀመረች። ሰዎችም ተደናግጠው ምንድነው የተፈጠረው ብለው ጠየቋት። እሷም ቦርሳዬን ጣልኩ ወይኔ ብሬ ውስጡ የሰው ገንዘብ አለ። ብላ በዝርዝር ማስረዳት ጀመረች።

ለመናፈስ ደርሳ የተመለሰችበት ቦታ ሲሄዱ ጠፋ የተባለው ቦርሳ የለም። መኪና ውስጥ ነው የጠፋው እንዳይባል ይዤ ነው የወረድኩት ብላ አስረድታለች። በዚህ ሁኔታ ትንሽ ከቆየን በኋላ እሷና አብረዋት የነበሩት ሰዎች ወደ መኪናው ተመልሰው ገቡ። መኪናውም ጉዞውን ቀጠለ። አጠገቧ የተቀመጠችው ሴትም ጉዳዩን በማስተዛዘን ትናገር ጀመር።

በዚህ መሐል አንድ ተሳፋሪ ከተቀመጠበት ተነስቶ እንዲህ አለ፦

“ሰዎች ይህች ሴት ቦርሳዋን በድንገት ጥላለች። ውስጡ የሰው ገንዘብ አለ ብላለችና ያለንን እናዋጣላት። ያለንን በማዋጣት እንደግፋት” አለ። በዚህም መሰረት ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ፥ ተሳፋሪዎቹ ያላቸውን አዋጡላት።

ገንዘቡም ከአምስት መቶ ብር በላይ ደረሰ። ብሩም ተሰጣት። ቦርሳ የጠፋባት ሴትም ደስተኛ ሆነች። ሁሉንም ማመስገን ጀመረች።

ችግሩ በመፈታቱና ጉዟችንን በመቀጠላችን ሁሉም ደስተኞች ይመስላሉ። በዚህ ሁኔታ ጥቂት ከተጓዝን በኋላ ያችው ሴት አጠገቧ ካለችው ጋር መጨቃጨቅ ጀመሩ። ነገሩ የሚበርድ ነው ብለን ችላ ብንልም ቀስ በቀስ ግን እየተካረረረ መጣ። በዚህ ጊዜ ነበር ከፊታቸውና ከኋላቸው ያሉ ሰዎች የመገላገል ስራ የጀመሩት። ይሁን እንጂ በተለይ ቦርሳ የጠፋባት ሴት አጠገብ የተቀመጠችው ሴት በኃይል ትናገር ነበር። ነገሩ በመካረሩ እጅ ለእጅ ሲያያዙ አሽከርካሪው መኪናውን ለማቆም ተገደደ። እንደምንም ተገፍተው ከመኪናው ወረዱ። ተሳፋሪዎችም የነገሩን ፍፃሜ ለማወቅ አብረው ወረዱ።

በዚህ ጊዜ ነበር ያች ቦርሳ ከጠፋባት ሴት ጋር የተጋጨችው ሴት ጉዱን የዘረገፈችው። “የጠፋ ቦርሳም ሆነ ብር የለም። በዚህ መንገድ ተነጋግረን እኩል ለመካፈል ነበር የተስማማነው። አሁን ብሩ እጇ ሲገባ ቃሏን አጠፈች። የጥላችን መንስኤ ይሔ ነው” አለች፤ ያለ ፍርሃት፤ ያለ ሃፍረት።

በሁለት ሰው ጥል ምክንያት በመንገላታታቸው ሲበሳጩ የነበሩት ተሳፋሪዎች ሁሉ በጉዳዩ ባለቤትነት ላይ ተጠመዱ። ብዙዎቹ በጣም ተበሳጩ። የሰው ገንዘብ መውሰድ ለምን አስፈለገ? ብለው አጉረመረሙ። መሰል ሃሳቦች ከሁሉም ይሰነዘሩ ነበር።

በኋላም የመኪናው አሽከርካሪ ነገሩን ሰብሰብ አድርጎ ሁሉም ወደ መኪናው እንዲገቡ አሳሰበ። ምንም እፍረት የማይታይባቸው ሴቶቹም ከተሳፋሪው ቀድመው ወደ መኪናው ገቡ። ከዚያም አሽከርካሪው “ጉዳዩ አሳፋሪ ነው። እውነት መስሎን አምነን እንጂ ተርፎን አልሰጠንም። ስለዚህ ገንዘቡን ለሰበሰበው ሰው ታስረክቢያለሽ። የሰበሰበውም ሰው ለተቀበለው ይመልሳል እናንተን ወደ ህግ አካል አደርሳችኋለሁ” ብሎ ተናገረ። በዚህ ጊዜ ለመንገዱ የቸኮለው ተሳፋሪ ሁሉ በነገሩ ቢበሳጭም በሃሳቡ ግን ተስማማ።

ሳትወድ በግድ ገንዘቡን ከሰው ሰብስቦ ለሰጣት ተሳፋሪ አስረከበች። እሱም ቆጥሮ ተረከባት። ከዚያ የተዋጣውን ገንዘብ ለባለቤቶቹ መለሰ።

ምን አለበት ሰርቶ ማግኘት እየተቻለ ውርደት ውስጥ ባትገባ፥ የሚሉ ሃሳቦች አሁንም ከተሳፋሪው ይደመጡ ነበር። “እውነት ነው የሰው ልጅ መስራት እየቻለ ለምን የሰውን ገንዘብ ባልተገባ መንገድ ለማግኘት የሚሯሯጠው? ሰርተህ ብላ እንጂ ሰርቀህ ብላ የሚል መርህ የለም” አለ አንድ ጎልማሳ።

ስርቆት ሁሌም አይሳካም። ምናልባት ሌላ ጊዜ ተሳክቶላት ሊሆን ይችላል። ቢሆንም በማጭበርበር የሚገኝ ገንዘብ የህሊና እረፍትን አይሰጥም። ምናልባት የማጭበርበሪያ ስልቶቹን በጊዜው ሰዎች ባያውቁም ከህሊና ክስ ማምለጥ ግን አይቻልም።

እንደ አጋጣሚ ሆኖ እነዚህ ሴቶች ዛሬ በእንዲህ አይነት መልኩ ተጋልጠዋል። በሌላ በኩል እነዚህ ተሳፋሪዎች በሌላ ጊዜ ሰው የእውነት ቢቸገር እንኳን መስጠት እንዳይችሉ ወይም እንዲጠራጠሩ የሚያደርግ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ አጋጣሚ ነው። ስለዚህ መስራት የሚችል ሰርቶ ማግኘት አለበት።

ከዚህ ሁኔታ በኋላ ሰዎች እርስ በራስ ሳይጨዋወቱ መኪናው በዝምታ መጓዙን ቀጠለ። ረፋድ እንገባለን ብሎ የጓጓው ተሳፋሪም ቀትር ላይ ሶዶ መናኻሪያ መድረስ ችሏል። ተሳፋሪዎችን መናኻሪያ ካወረደ በኋላ ሁለቱን ሴቶች ወደ ፖሊስ ጣቢያ ለመውሰድ መኪናው ከቅጥር ጊቢው ወጣ።