“ባለፉት ሰባት ዓመታት የክልሉ ገቢ የመሠብሰብ አቅም ከ7 ቢሊዮን ብር ወደ 13 ቢሊዮን ብር አድጓል” – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
“ባለፉት ሰባት ዓመታት የክልሉ ገቢ የመሠብሰብ አቅም ከ7 ቢሊዮን ብር ወደ 13 ቢሊዮን ብር አድጓል” ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ገቢን ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ መስራት እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በሴክቶሪያል ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የክልሉን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ገቢን ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ መስራት ይገባል ብለዋል።
የውስጥ ገቢን በአግባቡ በመሠብሰብ ወጪን መሸፈን የጠንካራ መንግስት መገለጫ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉን ፀጋ ተጠቅሞ አዳጊ ለሆነው የልማት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ገቢን ተቀናጅቶ መሠብሰብ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ባለፉት 7 አመታት የኢኮኖሚ ሴክተር ላይ በተደረገ ሪፎርም የክልሉ ገቢ የመሠብሰብ አቅም ከ7 ቢሊዮን ብር ወደ 13 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ማስቻሉን ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን አብራርተዋል።
በቀጣይ ገቢ ያልተሰበሰበባቸውን የገቢ ርዕሶች እና ለገቢ አሰባሰብ ማነቆ የሆኑ ተግዳሮቶችን በመለየትና በመፍታት በ2018 የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ ርብርብ ሊደረግ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በርካታ የልማት ጥያቄዎች መኖራቸውን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን፤ ምላሽ ለመስጠት ገቢን አሟጦ መሰብሰብ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ፍትሃዊና ተዓማኒ የሆነ ገቢ መሠብሰብና ማነቆዎችን መፍታት የአመራሩ ቁልፍ ተግባር ሊሆን ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ፍርድ ቤቶች የገቢ ህጉን በማስከበር ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
ገቢ መሠብሰብ የአንድ ተቋም ተግባር ብቻ አለመሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸው ሊወጡ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የታችኛው መዋቅሮች የድጎማ በጀት ላይ ከመንጠልጠል ባሻገር የውስጥ ወጪያቸውን ለመሸፈንና ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ለማድረገ ገቢን በአግባቡ መሠብሰብ እንደሚገባቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ደመቀ በበኩላቸው፤ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በማዘመን ግብር ከፋዮች በኢ-ፋይሊንግ፣ ኢ-ፔይመንት እና የቴሌብር ክፍያ አገልግሎት ተጠቅመው ግብር እንዲከፍሉ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
መንግስት ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ያሉት ኃላፊዋ፤ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዲሰፋ እና ገቢ የመሰብሰብ አቅም እንዲያድግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
እንደ ክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ፤ በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 19 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ የዕቅዱን 90 በመቶ ማሳካት መቻሉንም የቢሮ ኃላፊዋ ተናግረዋል።
የታክስ ስርዓቱ ውጤታማነትን አዳጊ ከሆነው የህዝብ የልማት ፍላጎት ጋር እና የመንግስት ወጪ ፍላጎት ጋር ለማጣጣም ቀሪ ብዙ ተግባራት ያሉ በመሆናቸው የጋራ ርብርብ ይጠይቃል ሲሉም አሳስበዋል።
ተቋሙ ከሌብነትና ብልሹ አሰራር የፀዳ ሆኖ በመልካም ስነ ምግባር የተገነባ አገልግሎት አሰጣጥ መገለጫው እንዲሆን በርካታ ሥራዎችን እየተከናወኑ እንደሚገኝም ወ/ሮ አለምነሽ አብራርተዋል።
በቀጣይ የሴክተሩ የ2017 በጀት ዓመት ማጠቃለያ አፈፃፀም ቀርቦ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
More Stories
በዞኑ በበልግና በመኸር ወቅት የተከናወኑ የግብርና ስራዎች የተሻለ ውጤት መታየቱን የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለጹ
የግብርና ዘርፍ የእሴት ሰንሰለትን በመከተል የስራ ዕድልን መፍጠር በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ገለፀ
በጥረቱ ውጤታማ የሆነው ወጣት ተሞክሮ!