በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በቱርካና ሐይቅና በኦሞ ወንዝ ሙላት ለተፈናቀሉ ተማሪዎች የተለያዩ ተቋማትና ድርጅቶች የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረጉ

በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በቱርካና ሐይቅና በኦሞ ወንዝ ሙላት ለተፈናቀሉ ተማሪዎች የተለያዩ ተቋማትና ድርጅቶች የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረጉ

ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን (COC) የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት በዳሰነች ወረዳ በውሃ ሙላት ምክንያት ለተፈናቀሉ አርብቶ አደር 500 ተማሪዎች ለሁለተኛ ዙር 416 መማሪያ ደብተርና 1,418 እስኪሪቢቶ ለወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት አስረክቧል።

ቱርካና ሐይቅ እና ኦሞ ወንዝ ሞልተው ወደኋላ በመፍሰሱ የውኃ መጠኑ ከወትሮው በተለየ መልኩ በመጨመሩ ዜጎችን ከቀያቸው አፈናቅሏል፤ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ከጥቅም ውጭ አድርጓል፡፡

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ፤ ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን (COC) የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና we action የተባሉ ግብረሰናይ ድርጀትና ተቋማት በተፈናቃዩ ማህበረሰብ አካባቢ በትምህርት ዘርፍ የሚታዩ ውስንነቶችን ለመቅረፍ የትምህርት ግብአቶችንና መማሪያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጋቸውን የዳሰነች ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሄኖክ ግዛው አስታውቀዋል።

በኦሞ ወንዝ ሙላት ምክንያት በዳሰነች ወረዳ ለተፈናቀሉ 500 ተማሪዎች ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን ለሁለተኛ ዙር 416 ደርዘን ደብተርና 1,418 እስኪሪቢቶ ድጋፍ ማድረጉን የገለፁት በሴንተር ኦፍ ኮንሰርን (COC) የጂንካ አካበቢ የተቀናጀ የትምህርትና ህጻናት ጥበቃ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አማኑኤል ማቴዎስ፤ ድርጅታቸው ከሴቭ ዘ ችልድረን ጋር በመተባበር በዞኑ ሐመር፣ ዳሰነችና ኛንጋቶም ወረዳዎች እየተገበረ ባለው የተቀናጀ የትምህርትና ህጻናት ጥበቃ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ለሆኑ 1,439 የቅደመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎችና ህጻናት ቦርሳ፣ ደብተር፣ እርሳስ ጨምሮ የትምሀርት ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

በቀጣይም ድርጅቱ የመምህራንን አቅም ለማብቃትና ትምህርት ቤቶችን ለተማሪዎች ምቹ የማድረግ ስራን ከዞኑ አስተዳደርና ከትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አቶ አማኑኤል አረጋግጠዋል።

በድጋፍ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት በደቡብ ኦሞ ዞን ትምህርት መምሪያ የፈተና ክፍል አስተባባሪ አቶ አወቀ ተሾመ በትምህርት ዘርፍ ላይ የኦሞ ወንዝ ሙላት እያስከተለ ያለውን ጫና በመገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ድርጅቶችንና ተቋማትን አመስግነው ጥራት ያለውን ትምህርት ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የሚደረገውን ጥራት ሁሉም ማህበረሰብ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በአካባቢው የውኃ ሙላት አደጋ በወረዳው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ከአገልግሎት ውጭ ማድረጉን ተከትሎ ጊዜው ትምህርት ቤቶች ለሚመሩ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስና ግብአቶች ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።

ዘጋቢ: ጄታ ታገሠ – ከጂንካ ጣቢያችን