በጥንት አባቶች ተጠብቆ የቆየውን የጌዴኦ ባህላዊ መልክአ ምድር ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር በትኩረት እየተሠራ ነው
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፍሎር ፕሮጀክት በዲላ ዩኒቨርሲቲ በመሬት አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት ስልጠና ሰጥቷል፡፡
በስልጠናው መክፈቻ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ምክትልና የደን ልማት ዘርፍ ኃላፊ ዮሴፍ ማሩ (ዶ/ር) እንደገለፁት የተሰጠው ስልጠና የጌዴኦ ባህላዊ መልክአ ምድርን በዘላቂነት በመጠበቅ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍን መሰረት ያደረገ ነው፡፡
በስልጠናው በዲላ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የተለያዩ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ምሁራን፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
በጥንት አባቶች ተጠብቆ የቆየው የጌዴኦ ባህላዊ መልክአ ምድር ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር ቢሮው በትኩረት እየሠራ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ሀብታሙ ተመስገን (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ በማህበረሰብ አገልግሎት ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማድረግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንቱ አክለውም፤ በዓለም የተመሰከረለትን ተራራማ አካባቢን ለእርሻ የመጠቀም የጌዴኦ ባህላዊ ጥበብ ለትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን ከባለድርሻዎች ጋር መነጋገር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ውስን የተፈጥሮ ሀብት የሆነውን መሬትን በተቀናጀ መልኩ በዘላቂነት በመጠቀም ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያደረጉት ውይይት መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፍሎር ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አለምበጁ ክፍሌ አብራርተዋል፡፡
የቡናና የእንሰት ልማትን ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የተፈጥሮን ደን መጠበቅ፣ መንከባከብ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሰፍን በማድረግ ቀጣይነት ያለውን ልማት ለማስፋፋት ፕሮጀክቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው ሲሉም አቶ አለምበጁ ገልፀዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ዘሪሁን ዓለሙና ጴጥሮስ ሎሌ ከስልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ ተግባር ላይ በማዋል የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
አርብቶ አደሩን ከእንስሳት ሀብት ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የእንስሳት ኤክስፖርት ማዕከላት እንደሚያስፈልጉ ተጠቆመ
በጌዴኦ ዞን የጤና መድህን አባል የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የይርጋ ጨፌ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ
ሃኪም ዚዬች ወደ ዋይዳድ ካዛብላንካ ለመዛወር ተስማማ