የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍን በቤት ሙከራ በማስደገፍ ተማሪዎች የተሻለ ዕውቀት እንዲያገኙ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ

የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍን በቤት ሙከራ በማስደገፍ ተማሪዎች የተሻለ ዕውቀት እንዲያገኙ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ

ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን (COC) ግብረሰናይ ድርጀትን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኣሪና በደቡብ ኦሞ ዞኖች ለሚገኙ ለተመረጡ ትምህርት ቤቶች ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገዙ የቤተ ሙከራ (የላብራቶሪ) መሣሪያዎች ድጋፍ አድርጓል።

ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን (COC) ከቅደመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ድረስ ለተማሪዎች ምቹ አካባቢ ለመፍጠር ያለመ ትምህርት ቤት ግንባታና የትምህርት ግብአቶችን በማሟላት እንዲሁም የትምህርት ዘርፍ ባለሙያዎችንና መምህራንን የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እየሰጠ የሚገኝ ግብረሰናይ ድርጀት ነው።

በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሴንተር ኦፍ ኮንሰርን ድርጅት የጂንካ አካባቢ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አስማማው አስረስ እንደገለፁት፤ ፕሮጀክቱ ለ9 አመታት በትምህርት ዘርፍ ላይ እየሰራ መቆየቱን አንስተው የቤተ ሙከራ መሣሪያዎችና ኬሚካሎች በኣሪ ዞን ባካደወላና በጂንካ ከተማ 10 ትምህርት ቤቶች በደቡብ ኦሞ ዞን በናፀማይ ወረዳ 13 ትምህርት ቤቶች ከዚህ በፊት ድጋፍ ከተደረገው ጋር 27 ትምህርት ቤቶች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን ተናግረዋል።

አቶ አስማማው አክለውም፤ ድርጅታቸው ከዚህ ቀደመ ለ60 የኬሚስትሪ፣ የባዮሎጂና የፊዚክስ መምህራን ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመው ከንድፈ ሃሳብ ትምህርት በተጨማሪ ዘመኑ በሚፈለገው ደረጃ ሳይንሳዊ የፈጠራ ዕውቀቶችን ለተማሪዎች በቤተ ሙከራ በመታገዝ የተሻለ ዕወቀት እንዲያገኙ በማለም ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተገዙ ኬሚካሎችንና መሣሪያዎችን ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊዎችና የትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራን በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ በቤት ሙከራ በማስደገፍ ተማሪዎች የተሻለ ዕውቀት እንዲያገኙ የሚያስችል ድጋፍ መሆኑን አንስተው ድርጅቱ በትምህርት ጥራት ማሻሻልና በትምህርት ተቋማት የሚታየውን የግብአት ውስንነት ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ድጋፍ በመሆኑ ከልብ እናመሰግናለን ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

ዘጋቢ፡ ጄታ ታገሠ – ከጂንካ ጣቢያችን