ኤርሊንግ ሀላንድ 50 ጎሎች ላይ ፈጥኖ የደረሰ ተጫዋች ሆነ

ኤርሊንግ ሀላንድ 50 ጎሎች ላይ ፈጥኖ የደረሰ ተጫዋች ሆነ

ኖርወዌያዊው አጥቂ ኤርሊንግ ሀላንድ በብሔራዊ ቡድን ጨዋታ በጥቂት ጨዋታዎች 50 ጎል ላይ የደረሰ ቀዳሚው ተጫዋች ሆኗል።

ኖርወይ ትናንት ምሽት በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ  እስራኤልን 5ለ0 በረታችበት ጨዋታ ኤርሊንግ ሀላንድ 3 ጎሎችን በማስቆጠር ሃትሪክ መስራት ችሏል።

በዚህም ኤርሊንግ ሀላንድ ለብሔራዊ ቡድኑ ተሰልፎ በተጫወተባቸው 46 ጨዋታዎች ያስቆጠረውን የጎል ብዛት 51 አድርሷል።

ይህንን ተከትሎ የኖርዌይ ብሔራዊ ቡድን የምንግዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪው ሀላንድ በጥቂት የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች 50 ጎሎች ላይ የደረሰ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል።

ከዚህ ቀደም የክብረወሰኑ ባለቤት ሀሪ ኬን የነበረ ሲሆን ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን 50 ጎሎችን ለማስቆጠር  71 ጨዋታዎች አስፈልገውት ነበር።

ክሊያን ምባፔ እና ሮበርት ሌቫንዶውስኪ ደግሞ በ90 ጨዋታዎች ነው 50 ጎሎችን ለሀገሮቻቸው ማስቆጠር የቻሉት።

የ8 ጊዜ የባሎንዲኦር አሸናፊው ሊዮኔል ሜሲ ለአርጄንቲና ብሔራዊ ቡድን 50 ጎሎችን ለማስቆጠር 107 ጨዋታዎችን መጠበቅ ግድ ብሎት ነበር።

141 ጎሎችን በማስቆጠር በመላው ዓለም በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የምንግዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ የሆነው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በበኩሉ ለፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን 50 ጎሎችን ያስቆጠረው 114 ጨዋታዎችን ካከናወነ በኋላ ነው።

የ25 ዓመቱ ኤርሊንግ ሃላንድ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግም በጥቂት የጨዋታ ቁጥር 50 ጎል ላይ በመድረስ በሩድ ቫኔስትሮይ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን ከቀናት በፊት በእጁ ማስገባቱ አይዘነጋም።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ