ብሩኖ ፈርናንዴዝ ወደ ሳውዲ ፕሮ ሊግ የማቅናት ፍላጎት እንደሌለው ተገለፀ

የማንቸስተር ዩናይትዱ አምበል ብሩኖ በያዝነው ውድድር ዓመት መጨረሻ ወደ ሳውዲ ፕሮሊግ የማቅናት ፍላጎት እንደሌለው ተገልጿል።

ፖርቹጋላዊው የመሀል ሜዳ ተጫዋች ከሰሞኑ በቀጣይ ክረምት ከ23ኛው የዓለም ዋንጫ መጠናቀቅ በኋላ ቀያይ ሰይጣኖችን በመልቀቅ ወደ ከሳውዲ አረቢያ ክለቦች መካከል ለአንደኛው እግር ኳስ ክለብ ሊፈርም እንደሚችል ሲዘገብ ነበር።

ሆኖም ግን በእንግሊዙ ቀሪ የሁለት ዓመት ኮንትራት ያለው የ31 ዓመቱ ተጫዋች ማንቸስተር ዩናይትድን ቢለቅ እንኳን ወደ ሩቅ ምስራቅ ከመሄድ ይልቅ በታላላቅ የአውሮፓ ሊጎች የመጫወት ፍላጎት እንዳለው ቢቢሲ አስነብቧል።

በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ሁለቱ የሳውዲ ክለቦች አል ሂላል እና አል ኢቲሃድ ብሩኖ ፈርናንዴዝን ለማስፈረም ከፍተኛ የዝውውር ሒሳብ እና የደሞዝ ክፍያ ቢያርቡለትም ተጫዋቹ የቀረበለትን የዝውውር ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ አይዘነጋም።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 ከሀገሩ ክለብ ስፖርቲንግ ሊዝበን ማንቸስተር ዩናይትድን የተቀላቀለው ብሩኖ ፈርናንዴዝ ለላንክሻይሩ ክለብ እስካሁን 298 ጨዋታዎችን በማከናወን 100 ጎሎችን ከመረብ አሳርፏል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ