የሰርከስ ስፖርት ሳይንሳዊ ጥበቡን ጠብቆ ለማጎልበት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ

የሰርከስ ስፖርት ሳይንሳዊ ጥበቡን ጠብቆ ለማጎልበት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ

ቢሮው ያዘጋጀው የሰርከስ ስፖርት የአሰልጣኞች ስልጠና በሆሳዕና ከተማ እየተሰጠ ነው።

በአለም በ1768 በእንስሳቶች የጂምናስቲክ እንቅስቃሴ አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው የሰርከስ ስፖርት አሁን ላይ በሀገራችን ኢትዮጵያ በስፋት እየተለመደ ያለ ተወዳጅና ተፈቃሪ ስፖርት ሆኗል።

በስልጠናው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፋት የሀድያ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ምክትልና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ክብሩ ዮሃንስ፤ በሰርከስ ስፖርት ዘርፍ በስነ ምግባር፣ በአካልና አእምሮ የዳበረ ብቁ ዜጋ ለማፍራት የዘርፉን አሰልጣኞች አቅም ሳይንሳዊ የስፖርት ጥበብን ጠብቆ ማጎልበት ወሳኝ ድርሻ አለው ብለዋል።

ወጣቱን በስፖርት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን በስልጠናው መክፈቻ የተናገሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትልና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰይፈ አለሙ ናቸው።

የሰርከስ ስፖርት በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅና ተቀባይነቱ እየጨመረ የመጣ ተዘውታሪ ስፖርት መሆኑን የገለፁት አቶ ሰይፈ፤ እንደ ሀገር በዘርፉ የካበተ ልምድና እውቀት ባላቸው ኢንስትራክተሮች አማካኝነት ከክልሉ ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ አሰልጣኞች ወቅቱን የጠበቀ የክህሎትና ተግባር ልምምድ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።

ለስልጠናው ስኬታማነት የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ ላሳየው አጋርነት አመስግነዋል።

የብሔራዊ ሰርከስ ስፖርት ጥምረት ማህበር ተወካይና የአሰልጣኞች አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ቢኒያም ወርቁ በበኩላቸው፤ በሰርከስና ጂምናስቲክ ስፖርት ዘርፍ እንደሀገር አሁን ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አሰልጣኞችም በስልጠና ቆይታቸው ያላቸውን ዕውቀትና ልምድ የሚያዳብር ሳይንሳዊ ስልጠና እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል።

የሰርከስ ስፖርት የአሰልጣኞች ስልጠናው ከመስከረም 29 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 11/2018 ለተከታታይ 10 ቀናት ይቆያል።

ዘጋቢ: አብዱልሃሚድ አወል – ከሆሳዕና ጣቢያችን