የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት በ2018 በጀት ዓመት በኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ከዞኑ ንግድና ትራንስፖርት መምሪያዎች ጋር የህዝብ አስተያየት ማሰባሰቢያ መድረክ አካሄደ

የጌዴኦ ዞን የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባልና የዕለቱ የክብር እንግዳ ተወካይ አቶ በላይ ዳካ ባስተላለፈፉት መልዕክት፤ የውይይቱ ዓላማ በበጀት ዓመቱ የነዳጅ እጥረት ባጋጠመ ወቅት የነበሩ ችግሮችና አሁናዊ ሁኔታ፣ የህብረተሰቡን አስተዋጽኦ ጭምር መገምገምና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫን ማመላከት ነው ብለዋል።

‎የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጌዴኦ ዞን ዋና አፈጉባዔ ፀጋዬ ታደሰ፤ ውይይቱ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ማግስት መካሄዱ የተለየ እንደሚያደርገው አስታውሰው በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ ያለውን የአቅርቦት ማነስና የገበያ አለመረጋጋት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

‎የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የጌዴኦ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሠላማዊት ያሬድ፤ ነዳጅን በአቋም ያለመምራት እና ማኑፋክቸር ዘርፍ ከይርጋጨፌ ከተማ በስተቀር ተግባራዊ ያለመሆን በበጀት ዓመቱ ከታዩ ደካማ ጎኖች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በርካታ የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው የፍጆታ ዕቃዎችን ማስወገዳቸውንና በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

‎የዞኑ መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ስለሺ ሺፈራው፤ ከትራንስፖርት አገልግሎት ጋር ተያይዞ በበጀት ዓመቱ 4 ሺህ 7 መቶ በላይ አሽከርካሪዎች ደንብ በመተላለፍ መቀጣታቸውን ገልጸው እስከአሁንም ከቅጣት አለመማራቸውንና ህብረተሰቡም የአሽከርካሪዎች ተባባሪ የመሆን አዝማሚያ መኖሩን ነው የተናገሩት።

‎ከተሳታፊዎች መካከል ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ክንዱ፣ አቶ ደሳለኝ በቀለ እና ሌሎችም አቅርቦት እና ፍላጎት አንፃር አለመጣጣም፣ በሰንበት ገበያ ላይ የሚስተዋል የዋጋ ንረትና ጥራት፣ በትራንስፖርት ዘርፍም ከነዳጅ ጋር ተያይዞ የሚታዩ አለመረጋጋት ችግሮች በጥናት የተደገፈ ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

‎ተሳታፊዎቹ አክለውም ለደህንነት ሲባል በትርፍነት ከመጫን እና ከታሪፍ በላይ በመክፈል ለአሽከርካሪዎች ከመወገን የባህርይ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል ብለዋል።

‎የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት በ2018 በጀት ዓመት በኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ከዞኑ ንግድና ትራንስፖርት መምሪያዎች ጋር በመቀናጀት የህዝብ አስተያየት የጋራ መድረክ ላይ የዞኑ አፈ ጉባዔዎች፣ የንግድና ትራንስፖርት ኃላፊዎች፣ የፀጥታ አካላት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት በዲላ አተማ ተካሂዷል።

‎ዘጋቢ: ምርጫ መላኩ – ከይርጋ ጨፌ ጣቢያችን