‎የወጣቶቻችንን ያልተገደበ ምናብ እና የእጆቻቸውን ጥበብ ወደ ተጨባጭ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት መቀየር እንደሚገባ ተገለጸ‎

‎የወጣቶቻችንን ያልተገደበ ምናብ እና የእጆቻቸውን ጥበብ ወደ ተጨባጭ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት መቀየር እንደሚገባ ተገለጸ

‎ሀዋሳ: ሰኔ 05/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የወጣቶቻችንን ያልተገደበ ምናብ እና የእጆቻቸውን ጥበብ ወደ ተጨባጭ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለመቀየር ሳይንስና ቴክኖሎጂ የጎላ ድርሻ እንዳለው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ገለጹ።

‎3ኛው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሣይንስ፣ የፈጠራ ስራዎች ውድድርና አውደ ርዕይ በዛሬው እለት በቡታጅራ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡

‎“ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን የሣይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ማዕከል እናድርግ” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው ኤግዚቢሽንና አውደ ርዕይ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ፥ ያለ ሳይንሳዊ ግኝቶችና ያለ ቴክኖሎጂ ፈጠራ የምናልማትን የበለጸገች ኢትዮጵያም ሆነ ክልልም መገንባት አይታሰብም ነው ያሉት።

‎ይህ የሳይንስና ፈጠራ ሥራዎች ውድድርና ዓውደ-ርዕይ ክልሉ ከተመሠረተ ማግስት ጀምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው 2 ዙር ውድድሮች በርካታ አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦች የፈለቁበት፣ ባለተሰጥኦ ወጣቶች ብቅ ያሉበት እና በርካታ ተስፋ ሰጪ ምርቶች ለእይታ መብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

‎ዛሬ ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄደው ይህ ውድድር፥ ካለፉት ዓመታት እጅግ የላቁ፣ ይበልጥ ማህበረሰባዊ ችግሮችን በቀጥታ የሚፈቱ፣ ወደ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ተሻግረው የህዝባችንን የዕለት ተዕለት ህይወት ማሻሻል የሚችሉ ስራዎች መቅረባቸውን በተግባር የምናይበት ነው ብለዋል፡፡

‎የክልልና የሀገራችን የነገ ተስፋዎች በእጆቻችሁና በአዕምሯችሁ የያዛችሁት እያንዳንዱ የፈጠራ ስራ የክልላችንን ግብርና፤ አይሲቲ፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ጤና እና ትምህርት ዘርፍ ሊያዘምን የሚችል ትልቅ አቅም እንዳለው አመላክተዋል፡፡

‎በዘንድሮው ውድድር ዳኝነቱ ነፃ፣ ፍትሀዊና ገለልተኝነ-ለማረጋገጥና በብቃት ለመምራት ለዳኞችና ተወዳዳሪዎች የኮዲንግ ስርዓት ለመጀመርያ ጊዜ ከ166 በላይ ኮዶች ስራ ላይ መዋላቸው አስረድተዋል፡፡

‎ዳኞቻች ከዋቸሞ፣ ወልቂጤና ወራቤ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከክልሉ ፖሊቴክኒክ ኮሌጆ የተውጣጡ ዳኞች በሂደቱ እንደሚሳተፉ ጠቁመው፥አጠቃላይ ሂደቱ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲ (ASTU) የዘርፉ ምሁራን የቅርብ ክትትልና ድጋፍ የሚመራ በመሆኑ የተዓማኒነት ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

‎የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ባይሳ በዳዳ በበኩላቸው፥ የዓለም የምጣኔ መልካምድር እየቀየረ የሚገኘው አንዱ የዲጂታል ኢኮኖሚ መሆኑን ጠቁመው፥ የእነዚህ መሠረቱ ሣይንስና ቴክኖሎጂ መሆኑን አመላክተዋል።

‎ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን በዓለም ዙሪያ ለኢኮኖሚ ሽግግር ጠንካራ አንቀሳቃሽ ኃይሎች ናቸው ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው፥ እኛም ሀገር ከጥቂት አመታት ወዲህ ይህንኑ ማየት ጀምረናል ነው ያሉት።

‎ቴክኖሎጂ ምርትና ምርታማነት ያሻሽላል፣ ተወዳዳሪነት እዲያድግ ያደርጋል፣ ማህበራዊ ተግዳሮቶችን ይፈታል፣ ከድህነት መውጫና ከኋላ ቀርነት መላቀቂያ መሣሪያ ነው ብለዋል።

‎የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶክተር ባይሳ በዳዳ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ አየለች እሸቴ የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ እንዲሁም የሳይንስ ኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ፣ የስራ እድል ፈጠራ እና ኢንተር ፕራይዝ ልማት ቢሮ እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ የስራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።

‎የትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ አየለች እሸቴ እንደገለጹት
‎ሀገር በቀል እውቀትን ከዘመናዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር በማዋሀድ ችግር መፍታት ላይ ማተኮር ይገባል ብለዋል።

‎እንደዚህ አይነት ፕሮግራሞች የፈጠራ ስራዎችን ማሳያ ብቻ ሳይሆኑ የሀገራችንን ኢንዱስትሪ እና የዲጂታል ስርዓት መጻኢ እድል ለሚቀረጽበት መንገድ ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል።

‎መርሐ ግብሩን የክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ፣ እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ቢሮ በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን ለሁለት ቀናት ይካሄዳል።

‎ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ