ቶማስ ፓርቴ የዓለም ዋንጫ ቪዛ በመከልከሉ የጋና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የካናዳን መንግስት ወቀሰ
የጋናው አማካይ ቶማስ ፓርቴ በፍርድ ቤት ያልተቋጨ የመድፈር ወንጀል ክስ ምክንያት ካናዳ የዓለም ዋንጫ ቪዛ መከልከሉን አስታውቋለች፡፡
እንደ ኤፒ ዘገባ የጋና መንግስት አማካዩ ቶማስ ፓርቴ በመድፈር ወንጀል ክስ የፍርድ ቤት ሂደቱን እየተጠባበቀ ባለበት ወቅት፣ ለቡድኑ የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ወደ ካናዳ ለመግባት ያደረገውን የቪዛ ጥያቄ ውድቅ ማድረጓ “እጅግ ኢ-ፍትሃዊ” ነው በማለት የካናዳን ውሳኔ ኮንኗል። ውሳኔውን ለመቀልበስም ህጋዊ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ነው የገለጸው።
በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ በለንደን ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ የሚጠበቀው የ32 ዓመቱ ጋናዊው አማካይ ፓርቴ፥ ረቡዕ ዕለት በቶሮንቶ ከፓናማ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ ወደ ሀገሪቱ ለመግባት ያቀረበው የቪዛ ማመልከቻ በካናዳ ውድቅ ከተደረገበት በኋላ፣ በሮድ አይላንድ ወደሚገኘው የጋና የልምምድ ካምፕ ተመልሷል።
የጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ ካናዳ ለፓርቴ “የጊዜያዊ መኖርያ ፈቃድ (ቪዛ) ጥያቄን ለመከልከል የወሰደችው እርምጃ እጅግ ኢ-ፍትሃዊ ውሳኔ” ሲል ወቅሷል።
ፓርቴ ከ2020 እስከ 2025 በእንግሊዙ አርሰናል ክለብ በነበረበት ወቅት ከበርካታ ሴቶች የቀረቡበትን የወንጀል ክሶች መከላከሉን ተከትሎ ባለፈው የውድድር ዘመን በስፔኑ ቪላሪያል የተጫወተው ፓርቴ፣ በቀረበበት ክስ ላይ ጥፋተኛ አለመሆኑን አስታውቋል።
የጋና መንግስት በመግለጫው “ማንኛውም ሰው በህግ ፊት ጥፋተኝነቱ እስካልተረጋገጠ ድረስ እንደ ንጹህ የመቆጠር መሰረታዊ የህግ መርህን በድጋሚ ያረጋግጣል፤ ይህም በዲሞክራሲያዊ ማህበረሰቦች ውስጥ የፍትህ እና የህግ የበላይነት የማዕዘን ድንጋይ ነው” ብሏል።
“ካናዳ የኢሚግሬሽን ህጎቿን የማስከበር ሉዓላዊ መብቷን የምናከብር ቢሆንም፣ ፍርድ ቤት ውሳኔ ባልሰጠበት እና ባልተረጋገጠ ክስ ላይ ተመስርቶ የተላለፈው ውሳኔ ፍትሃዊነትንና ሚዛናዊነትን ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል” ሲል መግለጫው ያብራራል። “በመሆኑም ጋና በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው የካናዳ ባለስልጣናት ጋር የዲፕሎማሲ ንግግሮችን እያደረገች ትገኛለች።” ብሏል፡፡
የጋና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ካርሎስ ኬይሮስም ፓርቴን በዓለም ዋንጫ ስብስባቸው ውስጥ ሲያካትቱ፣ ይህንኑ “በህግ ፊት የመንጻት መብት” መርህ ጠቅሰው ነበር።
የጋና መንግስት ውሳኔው እንደገና እንዲታይ ለካናዳ “ይፋዊ የተቃውሞ ደብዳቤ” መላኩን ገልጿል። በተጨማሪም “በካናዳ እና በዓለም አቀፍ ህግ ስር ያሉትን ሁሉንም የዲፕሎማሲ፣ የህግ እና የአስተዳደር መፍትሄዎች፥ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ጉዳዩን ለካናዳ ፌዴራል ፍርድ ቤት በመውሰድ የዳኝነት ክለሳ (Judicial review) ማግኘትን ጨምሮ ጉዳዩ በህግ አግባብ ሙሉ እና ፍትሃዊ እይታ እንዲያገኝ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን” አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ከካናዳ ባለስልጣናት ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑንና ጋና ለጉዳዩ “በወቅቱ አወንታዊ መፍትሄ ለመስጠት” ከባልደረቦቿ ጋር ገንቢ ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን መግለጫው አክሎ አብራርቷል።
የፓርቴ ጠበቃ ባለፈው መጋቢት ወር እንዳሉት፣ አንዲት ሴት እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 2020 በአንድ ቀን ውስጥ ሁለት ጊዜ ደፍሮኛል በማለት ባቀረበችበት አዲስ ክስ ላይ ተጫዋቹ ጥፋተኛ አለመሆኑን በፍርድ ቤት ተከላክሎሎ የነበረ ቢሆንም፥ ቀደም ሲል ከሌሎች ሶስት ሴቶች ጋር በተያያዘ በአምስት የመድፈር ወንጀል እና በአንድ የጾታ ጥቃት ክስ ፍርዱን እየተጠባበቀ ነው፡፡ አዲሶቹ ክሶች የተሰሙት የመጀመሪያዎቹ ክሶች ይፋ ከሆኑ በኋላ ነው።
ፓርቴ ሰኔ 23 ጋና በማሳቹሴትስ ከእንግሊዝ ጋር ለምታደርገው ጨዋታ መሰለፍ ይችላል። ጋና የምድብ ጨዋታዋን ሰኔ 27 በፊላደልፊያ ከክሮሺያ ጋር በምታደርገው ጨዋታ ታጠናቅቃለች።
የጋና መንግስት በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ “ይህ ውብ የእግር ኳስ ጨዋታ ህዝቦችን የማስተሳሰር፣ ዘላቂ የወዳጅነት ትስስር የመፍጠር፣ በህገ-ደንብ የመጫወት እንዲሁም በሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጪ ፍትሃዊነትን የማስፈን ስሙን ጠብቆ እንዲቀጥል እንመኛለን” ማለቱን የዘገበው ኤፒ ነው።
በዘላለም ተስፋዬ

More Stories
አይዩብ ቡአዲ የአርሰናል ቀዳሚ ኢላማ ሆኗል!
ኦማር አርታ ከፊፋ ክፍያ ሊፈፀምለት ነው
የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ዝርፊያ ተፈፀመበት