ሰርጂዮ ቡስኬት ጫማውን ሊሰቅል ነው

ሰርጂዮ ቡስኬት ጫማውን ሊሰቅል ነው

ስፔናዊው የመሐል ስፍራ ተጫዋች ሰርጂዮ ቡስኬት እግር ኳስ መጫወትን ሊያቆም መሆኑን ገልጿል።

ለአሜሪካው ክለብ ኢንተር ሚያሚ እየተጫወተ የሚገኘው ቡስኬት የዚህ ዓመት የሜጄር ሊግ ሶከር ውድድር በጥቅምት ወር ሲጠናቀቅ በይፋ ጫማውን የሚሰቅል መሆኑን አሳውቋል።

የቀድሞ የባርሴሎናው የተከላካይ አማካይ በ37 ዓመቱ ነው እግር ኳስን መጫወት ለማቆም የወሰነው።

ከላማሲያ አካዳሚ የተገኘው ቡስኬት ለባርሴሎና ዋናው ቡድን እንደ አውሮፓውያኑ ከ2008 አንስቶ እስከ 2023 ድረስ ተጫውቶ ማሳለፉ ይታወቃል።

ለብሉግራናዎቹ 722 ጨዋታዎችን በማከናወን ብዙ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ በመጫወት ከሊዮኔል ሜሲ እና ዣቪ ሄርናንዴዝ በመቀጠል 3ኛው የክለቡ ተጫዋች ነው።

በካታላኑ ክለብ በነበረው ቆይታም 9 የላሊጋ ዋንጫዎችን እና 3 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ጨምሮ 32 ትልልቅ የዋንጫ ስኬቶችን አስመዝግቧል።

በ2023 የስፔኑን ክለብ በመልቀቅ ወደ አሜሪካ አቅንቶ ለኢንተር ሚያሚ በመፈረም ከቀድሞው የቡድን አጋሩ ሊዮኔል ሜሲ በድጋሚ አብሮ የመጫወት ዕድልን ያገኘው ቡስኬት ዴቪድ ቤካም በባለቤትነት ለሚያስተዳድረው ክለብ እስካሁን 69 ጨዋታዎችን አከናውኗል።

ሰርጂዮ ቡስኬት ለስፔን ብሔራዊ ቡድን 143 ጨዋታዎችን ያከናወነ ሲሆን ከላ ሮጃዎች ጋር 2 የአውሮፓ ዋንጫዎችን እና 1 የዓለም ዋንጫ ስኬቶችን ማጣጣም ችሏል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ