የ41 ዓመቱ ወጣት
ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ወደዚህች ምድር ከመጣ እነሆ ዛሬ 41 ዓመት ሆኖታል።
ዓለማችን ካፈራቻቸው ኮከብ እግርኳስ ተጫዋቾች ከግንባር ቀደሞች ተርታ የሚገኘው ሮናልዶ ለእግርኳስ የተፈጠረ ሰው ነው ብንል ማጋነን አይሆንም።
ከዚያች ከትንሿ መንደር ማዴራ ተነስቶ በመላው ዓለም በሚኖሩ የእግርኳስ ወዳድ ቤተሰቦች ልብ ውስጥ መንገስ የቻለ ጥበበኛ ነው።
በእግርኳስ ዓለም ስሙ በወርቅ ቀለም ተፅፎ ይገኛል።
የጥረት፣ጠንክሮ የመስራት እና የትጋት ተምሳሌት የሆነው ሮናልዶ “ዕድሜ ቁጥር ብቻ ነው” ባይ ነው።
እግርኳስ ከዕድሜ ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያለው ቢሆንም ዕድሜውን አሸንፎ በ41 ዓመቱ አሁንም የዓለማችን ውዱ ተከፋይ እግርኳስ ተጫዋች ሆኖ ይገኛል።
“ክብረወሰኖች እኔን ይከተሉኛል እንጂ እኔ አልከተላቸውም” ሲል የሚደመጠው ክርስቲያኖ ሮናልዶ እስካሁን ከ40 በላይ የሆኑ የተለያዩ ዋና ዋና ክብረወሰኖችን በእጁ አስገብቷል።
ከእነዚህ መካከል 16 የሚሆኑት በጊነስ ወርልድ ሪከርድ ከእግርኳስ ህይወቱ ጋር የተያያዙ ክብረወሰኖች ተመዝግበዋል።
እስካሁን ካስመዘገባቸው ክብረወሰኖች ውስጥ በብሔራዊ ቡድን ጨዋታ፣በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፣የሪያል ማድሪድ እና እንዲሁም በአጠቃላይ የዓለማችን የምንግዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ የሚባሉ ክብረወሰኖችን ይዟል።
እስካሁን 961 ጎሎችን ያስቆጣረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ አንድ የአውሮፓ ዋንጫ እና አምስት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ጨምሮ 33 ዋንጫዎችን ማሸነፍ ችሏል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ የአምስት ጊዜ የባሎንዲኦር ተሸላሚ መሆኑ ይታወቃል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና የሴቶች ሩጫ በሀዲያ ዞን በሆሳዕና ከተማ ተካሄደ
አርሰናል ሊድስን በመርታት ወደ አሸናፊነት ተመለሰ
ማክስ ዳውማን ከአርሰናል ጋር የስኮላርሺፕ ውል ተፈራረመ