አዳዲስ እሳቤዎችን መነሻ በማድረግ ለበርካታ ስራ ፈላጊዎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እየሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዳዲስ እሳቤዎችን መነሻ በማድረግ ለበርካታ ስራ ፈላጊዎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እየሰራ መሆኑ ተገለጸ

‎በ2018 በጀት ዓመት ከ367 ሺህ በላይ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ አስታውቋል።

‎የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ጋር በመቀናጀት የአቅም ግንባታ ሥልጠና በአርባምንጭ ከተማ ሰጥቷል፡፡

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የከተማ ስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኦኬ ቦሌ፤ ስልጠናው ለአንድ ማዕከል አስተባባሪዎችና ፈጻሚ ባለሙያዎች በቀጣይ ትልቅ የሥራ አቅም የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል።

‎ኢ-መደበኛ አሰራሮችን ወደ መደበኛ አሰራር ከማሸጋገር ባሻገር አስራርን የማዘመን ስራ እየተሰራ ይገኛል ያሉት አቶ ኦኬ፤ በ2018 በጀት ዓመትም ከ367 ሺህ በላይ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

‎አዳዲስ እሳቤዎችን መነሻ በማድረግ ለበርካታ ስራ ፈላጊዎች የስራ ዕድል ለመፍጠር የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አቅዶ እየሠራ እንደሆነ የገለፁት ደግሞ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የስራ ዕድል ፈጠራ ማስፋፊያ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘሪሁን አለማየሁ ናቸው።

‎ከዚህ በፊት “አንድ ማዕከል” ተብሎ ሲጠራ የነበረዉ “የሥራ ማዕከል” ተብሎ ሪፎርም መደረጉንና ይህም የሥራ ፈጠራ ባለቤቶች የሚፈጠሩበት ማዕከል ነዉም ብለዋል።

‎የእሴት ሰንሰለትን መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ ኢ-መደበኛ ኢኮኖሚዉን ወደ መደበኛ ማሸጋገር እና ዲጂታል ቴክኖሎጂን መጠቀም ላይ ተግተዉ መሥራት እንደሚገባቸዉ አስገንዝበዋል።

‎የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ስልጠናው በዕውቀት መረዳትን የፈጠረ፣ በቀጣይም ማሰልጠን እንዲችሉ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

‎ስልጠናው በክልሉ በሚገኙ 192 አንድ ማዕከላት አስተባባሪዎችና ለሞዴል ፈጻሚ ባለሙያዎች በተለያዩ መመሪያዎችና ማኑዋሎች ዙሪያ ተሰጥቷል።

‎ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን