በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የልማት ተግባራት ተጠቃሚ መሆናቸውን በካፋ ዞን የገዋታ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ

በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የልማት ተግባራት ተጠቃሚ መሆናቸውን በካፋ ዞን የገዋታ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ

ድርጅቱ ላለፉት 20 ዓመታት በወረዳው ከ500 ሚሊየን ብር በላይ መድቦ ሲሰራ መቆየቱን አስታውቋል።

ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ ላለፉት 20 ዓመታት በርካታ ስራዎችን ያከናወነ ሲሆን፤ በወረዳው የነበረው ቆይታ ማጠናቀቂያ ፕሮግራም ተደርጓል።

ወይዘሮ አስቴር አበበ እና ወጣት ናጂ አወል፤ ድርጅቱ ለማህበረሰቡ በጎ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል።

ወይዘሮ ከሬነሽ ቆጭቶ እና አቶ ምትኩ ወልደማርያም፤ በድርጅቱ ድጋፍ የትምህርት ዕድል ማግኘታቸውን አስረድተው አሁን ደግሞ ለልጆቻቸው የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ በሰራው የመስኖ ልማት በግብርናው ዘርፍ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በምርጥ ዘር አቅርቦት፣ በንብ ማነብና በሌሎችም ዘርፎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ ያገኙትን ተሞክሮ ለሌሎች እያጋሩ እንደሆነም አክለዋል፡፡

ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የህጻናትን ህይወት ለማሻሻልና ጤናማ ሕይወት እንዲኖራቸው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የድርጅቱ የኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ጥላሁን አስታውቀዋል፡፡

በወረዳው ከ1997 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ከ500 ሚሊየን ብር በላይ በመመደብ በርካታ ሥራዎችን በመስራት ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል፡፡

በሚቀጥሉት ጊዜያት በሚኖሩ ፕሮግራሞና እቅዶች ዞኑን ብሎም ክልሉን በማካተት አብሮ ለመስራት ድርጅቱ ፍላጎት እንዳለውና ውጤቱ በጥናት ተለይቶ የሚገለጽ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለ20 ዓመታት በገዋታ አካባቢ በፕሮግራሙ የተሰሩ የልማት ተግባራት ህዝባዊ መሰረት የያዙና ወረዳው የተረከባቸው በመሆናቸው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን