በጎፋ ዞን ያለውን ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት ለላቀ የቱሪስት መስህብነት ለማዋል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው – ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

በጎፋ ዞን ያለውን ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት ለላቀ የቱሪስት መስህብነት ለማዋል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው – ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

ሀዋሳ፡ መስከረም 15/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን ያለውን ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት ለላቀ የቱሪስት መስህብነት ለማዋል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን በኢፌዲሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የጎፋ ጋዜ ማስቃላ እና የኦይዳ ዮኦ ማስቃላ በዓልን ምክንያት በማድረግ የጎፋ ዞን አስተዳደር ከሳሮ ሃይኪንግ ጋር በመተባበር ኦይዳ ወረዳ ሳኣ ጉልኣ ተራራ ጉብኝት ተካሂዷል።

‎በዞኑ የሚገኘውን የሳኣ ጉልኣ ተራራ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

‎በኢፌዲሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ የጎፋ ጋዜ ማስቃላና የኦይዳ ዮኦ ማስቃላ ዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ የሳኣ ጉልኣ ተራራ ለመጎብኝት እይዳ ወረዳ ሳኣ ጉልኣ ተራራ ወጥተዋል።‎

ይሄ የጉዞ ማስታወሻ ለታሪክ ተመዝግቦ ሊቀመጥ እንደሚገባና በየዓመቱ በአደባባይ ከሚከበረው የጎፋ ጋዜና የኦይዳ ዮኦ ማስቃላ የዘመን መለወጫ በዓል ማግስት የሚጎበኝ የቱሪስት መስህብ ሥፍራ ይሆናል ብለዋል።‎

‎ዶክተር ተስፋዬ አክለውም፤ በአካባቢው የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት ዕቅድ የተያዘ መሆኑን ገልጸው፤ ተራራው አናት ላይ ሰገነት እንደሚገነባ፣ በጎፋ ልማት ማኅበር ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ እና የፕሮሞሽን ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።‎

ሳሮ ሀይኪንግ በዞኑ የሚገኘውን ተፈጥሮአዊ ስፍራዎችን ለማስተዋወቅ የሚያደርገውን ጥረት አድንቀዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ እንደገለፁት፤ የለውጡ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው ዘርፎች አንዱና ዋነኛው ቱሪዝም እንደመሆኑ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራ የሆነውን ሳኣ ጉልኣ ዣውሻ ተራራ ለማልማት አቅደን እየሰራን ነው።

የኦይዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታዘበ ጋቲሶ በበኩላቸው ሳኣ ጉልኣ ከሳውላ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን 202 ሄክታር ስፋት ያለውና ከባሕር ጠለል በላይ 1800 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራ ነዉ ብለዋል።

በጉብኝቱ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የሶዶ ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ፣ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እንጂነር ዳግማዊ አየለ፣ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የጎፋ ዞን አስተባባሪ አካላት፣ የጎፋ ዞንና የተለያዩ መዋቅሮች የካቢኔ አባላት፣ የኦይዳ ወረዳ አመራር አካላት፣ የሣሮ ሀይኪንግ አባላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን