የመስቀል በዓል ገበያ በምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በመታየቱ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረገ በወላይታ ዞን የሶዶ ከተማ አንዳንድ ሸማቾች ጠየቁ

የመስቀል በዓል ገበያ በምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በመታየቱ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረገ በወላይታ ዞን የሶዶ ከተማ አንዳንድ ሸማቾች ጠየቁ

የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ በበኩሉ የምርት አቅረቦት እጥረት እንዳይከሰት 1 ሺ 5 መቶ ኩንታል በላይ ስኳር እንደቀረበ ጠቁሟል፡፡

በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ካነጋገርናቸው ነዋሪዎች መካከል ወ/ሮ አለሚቱ ግደቦ እና ወ/ሮ ሜሮን አላሮ፤ በበአል ገበያ የምርት አቅርቦት ቢኖርም የገበያ ሁኔታ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ በርበሬ፣ ዘይትና ቅቤ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋቸው መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

ከፋብርካ ምርቶች የሰኳርና ዘይት እንዲሁም የዳቦ ዱቀት ዋጋ መጨመሩን አንስተው፤ የዋጋ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረገ ጠይቀዋል፡፡

በሶዶ ከተማ አሮኒ ገበያ ማዕከል ልብስ ሰፊ የሆኑት አበባየሁ ታደሰና ተመስገን ከበደ የሽፎንና የባህል ልብስ ገበያ የዋጋ ጭማሪ በመኖሩ የደንበኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል።

የእርድ በሬ ገበያ ዝቅተኛ 60 ሺ ብር እየተሸጠ ያለ ሲሆን መካከለኛ ከ75 ሺ እስከ 80 ሺ እንዲሁም ከፍተኛ ዋጋ አንድ መቶ ሃምሳ ሺ ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል።

የወላይታ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ተወካይ ወ/ሮ መብራት ማቴዎስ ለብርሃነ መስቀል በዓል የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ እንዲደርሱ አስፈላጊው ቁጥጥር እየተደረገ እንዳለ አንስተው፤ ህብረተሰቡ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ሲመለከት ጥቆማ እንዲያደርግ ተናግረዋል፡፡

ለብርሃነ መስቀል በዓል የፋብሪካና የግብርና ምርቶች እጥረት እንዳይከሰት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን ያነሱት ወ/ሮ መብራት፤ ከፋብሪካ ምርቶች ከ1 ሺ 5 መቶ በላይ ኩንታል ስኳር በህብረት ሥራ በኩል እንደመጣ ገልፀው ዘንድሮ በመንግሥት በድጎማ መልክ የሚቀርበው ዘይት እንዳልገባ አስረድተዋል።

አንድ ኪሎ ስኳር አንድ መቶ ሰላሳ ብር እየተሸጠ ሲሆን ገበያውን ለማረጋጋት ከመንግሥት ድጎማ እንደተደረገበት ተናግረዋል።

የበዓላት መደራረብና የመንግስት ሠራተኞች ደመወዝ ማሻሻያ ተከትሎ በገበያ ላይ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከልም ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንዳለ ወ/ሮ መብራት ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ድርሻዬ ጋሻው – ከዋካ ጣቢያችን