“ስራ ወደአንተ አይመጣም፤ ወደ ስራው ሂድ”
በደረሰ አስፋው
በርካቶች ከሰለጠኑበት የሙያ መስክ ውጭ ሌላ ስራ ያለ አይመስላቸውም። ዋናው ችግር ደግሞ የውስጥ ፍርሃት ነው። እከስራለሁ አለያም አልችልም የሚለው ደግሞ ቀዳሚውን ስፍራ ሊይዝ ይችላል። በዚህም በርካታ አመታት ያለስራ በመቀመጥ ጊዜያቸውን ያባክናሉ፡፡ ሌሎች የስራ አማራጮችን የመረጡት ግን በስኬት ጎዳና ላይ አልፈው ለብዙዎች አርአያ መሆን ችለዋል። በዚህም እችላለሁ የሚል ዕምነት አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም የዛሬዋ የዕቱ መለኛ የህይወት ተሞክሮ ማሳያ ነው፡፡
ወይዘሮ ተስፋነሽ አበበ ይባላሉ፡፡ በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ውሃ ምኝጭ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ የ“ስላንች ብሎኬት ማምረቻ” ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ብሎኬት ማምረት እንደገቡ ይናገራሉ፡፡ ከብሎኬት በተጨማሪ ቴራዞ፣ ሌሎች ቱቦዎችን ጨምሮ የግንባታ ግብአቶችን ያመርታሉ፡፡
ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ወደ ስራው ሲሰማሩ በ50 ሺህ ብር ካፒታል መነሳታቸውን ያነሳሉ፡፡ ዛሬ ግን በንብረት ላይ ያለውን ሳይጨምር ከ5 እስከ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት ካፒታል ስለማፍራታቸው ይናገራሉ፡፡ ብሎኬትና ሌሎች የግንባታ ግብአቶችን የሚያመርቱባቸው ዘመናዊ መሳሪዎችም ባለቤት ናቸው፡፡
እዚህ ስራ ላይ ከመሰማራታቸው በፊት ምንም ስራ እንዳልነበራቸው ነው የገለጹልኝ፡፡ ይሁንና ቀደም ብሎ በህክምናው ዘርፍ በነርሲንግ ሙያ ተመርቀው ነበር፡፡ በተመረቁበት የሙያ መስክ ግን ስራ ማግኘት አዳገታቸው፡፡ የቤት እመቤት ሆነው አመታት ተቆጠሩ፡፡ ያም ሆኖ ግን ስራ ከመፈለግ አልቦዘኑም፡፡ በሰለጠኑበት ሙያ ስራ ፍለጋ ከመስሪያ ቤት መስሪያ ቤት እየተዘዋወሩ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን ያለመታከት ተመልክተዋል፡፡
አንድ ቀን ግን “ውጤት ባልታየበት ፍለጋ ጊዜ ማባከኑ ለምንድነው? የሚል ጥያቄ ወደ አእምሮየ መጣ” ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፍርሃት ተገዳዳሪያቸው ሆነ፡፡ በሁለት ሀሳቦች ውስጥ ሆነው ወዲህና ወዲያ ሲዋልሉ ቆዩ፡፡ ለዚህ መላ ነው ባሉት ጉዳይ ዙሪያ ከባለቤታቸው ጋር መመካከሩን መረጡ፡፡
አማራጭ ሀሳባቸው የባለቤታቸውን ይሁንታ አገኙ፡፡ ቀድሞውኑ ስራ የሚጀምሩበት ሀሳብ የነበራቸው ባለቤታቸው በሀሳቡ ዙሪያ መግባባት መቻላቸው ለፍርሃታቸው ሁነኛ መድሃኒት ሆናቸው፡፡
ወይዘሮ ተስፋነሽ ጊዜ አላጠፉም። ባለቤታቸውንና ወንድማቸውን አስተባብረው ወደ ብሎኬት ማምረት ስራ ገቡ፡፡ ሲታገላቸው የነበረው ስራ የመጀመር ፍርሃት ከመወገዱ አልፎ ለ34 ሰራተኞችም የስራ ዕድል ፈጠሩ፡፡ ለአንድ ሰራተኛ በወር ከሶስት እስከ አራት ሺህ ብር የሚከፍሉበት ደረጃ ተሸጋገሩ፡፡
ወይዘሮ ተስፋነሽ በስራው መሰማራታቸው ብዙ ጥቅም እንዳስገኘላቸው ነው የተናገሩት። ለስራቸው አገልግሎት የሚሰጥ የጭነት መኪና ገዝተዋል፡፡ የኑሮ ዘይቤያቸው መቀየሩም እንዲሁ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በ50 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ወደ ስራው ሲገቡ የገበያ ማፈላለጉንም አብረው ይሰሩ ነበር፡፡ “ስራ ወደ አንተ ብቻ እንዲመጣ አትጠብቅ ወደ ስራውም መሄድ ይገባል” የሚሉት መለኛ ሴት ገበያ ወዳለበት ይሄዳሉ እንጂ ፈልገውኝ ይመጣሉ በሚል ተቀምጠው አይጠብቁም፡፡
የግንባታ ተቋማትን በር እያንኳኩ የስራዎቻቸውን ውጤቶች ያስተዋዉቃሉ። ምርቶቻቸውን ለገዟቸውም በራቸው ድረስ እያቀረቡ በርካታ የግንባታ ተቋማት ደንበኞችን አፈሩ፡፡ አዲስ የስራ አስተሳሰብን አስተዋወቁ። ይህ ያልተለመደ አሰራር በመሆኑ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን ተቸራቸው፡፡ በዚህም ገበያውን እየተቆጣጠሩ ሄዱ፡፡
ከራሳቸው የንግድ ተሞክሮ በመነሳት በአብዛኞች ነጋዴዎች የሚደረገውን ንግድ መተቸታቸው አልቀረም፡-
“የአብዛኞቻችን የንግድ ባህል ደካማ ነው ቢባል ድፍረት አይሆንብኝም፡፡ በአንድ ቦታ ተወስነን ገበያው እራሱ ወደኛ እንዲመጣ እንጠብቃለን፡፡ ይህ አሰራር ደግሞ ተወዳዳሪ ወይም ውጤታማ ሊያደርገን አይችልም። ከዚህ ይልቅ ወደ ገበያውም መሄድ እንደሚያስፈልግ መዘንጋት የለበትም፡፡ እኔም ገበያው ይመጣል ብሎ ከመጠበቅ ወደ ገበያዎቹ መሄዴ ተጠቃሚ አድርጎኛል፡፡
“ውጤት ያለጥረት አይገኝም፡፡ በዚህም ብዙ ዋጋ ከፍያለሁ፡፡ በከፈልኩት ድካም ልክ ደግሞ ውጤት አግኝቻለሁ፡፡ ለሌሎች ሰዎችም ሀሳብ መፍጠር የሚያስችል ልምድ ቀስሜበታለሁ፡፡ ሴት አትችልም የሚለውን አስተሳሰብ ሰብሬያለሁ፡፡ በዚህም አልችልም የሚለው ፍራትና ስጋት ተወግዷል”፡፡
የሴቶች የባልን እጅ ብቻ አይቶ መኖርን ይነቅፋሉ ወይዘሮ ተስፋነሽ፡፡ ከስራቸው ጎን ለጎን በሚኖራቸው ማህበራዊ መስተጋብርም ሌሎች ሴቶችን ከማንቃትም አልተቆጠቡም። የስኬት ሚስጥሩ ፈተናን ተሻግሮ በጥረት የሚገኝ ስለመሆኑም ልምዶቻቸውን ለሌሎች ያጋራሉ፡፡
ወይዘሮ ተስፋነሽ ባመጡት ስኬትና አርያነት ያለው ተግባር የከተማ አስተዳደሩ እውቅና ሰጥቷቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ በላይ ሊደገፉ እንደሚገባቸው ጠቆም አድርገዋል፡፡ በተለይ የቦታ ጥበቱን እልባት ሊበጅላቸው እንደሚገባ በማሳሰብ፡፡
ስራቸውን ለማዘመንና አቅርቦቱንም ለማሳደግ በሚል በቅርቡ ዘመናዊ የብሎኬት ማምረቻ ማሽን ማስገባታቸውንም ገልጸውልኛል፡፡ ከልማት ባንክ ጋር በገቡት የብድር ውል መሰረት ዘመናዊ የሆነ የሊዝ ማሽን አምጥተዋል፡፡ ምንም እንኳ ከገጠማቸው የቦታ ችግር የተነሳ ወደ ስራ መግባት ባይችልም፡፡
ከልማት ባንክ በሊዝ ያመጡት የብሎኬት ማምረቻ ማሽን በቀን እስከ መቶ ሰራተኛ በስራ ላይ ማሰማራት እንደሚችል ተናግረዋል። ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥረው ይህ የማምረቻ ማሽን ግን ያለስራ ተቀምጧል እያሉ ነው። እንደተመለከትኩትም ዘመናዊ እና በአንድ ጊዜ ብቻ በርካታ ብሎኬቶችን ማምረት የሚችለው ማሽን እንደተሸፈነ መቆሙን ተመልክቻለሁ፡፡ ችግሩ ከማምረቻ ቦታ ጥበት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡
ወይዘሮ ተስፋነሽም በርካታ ስራ አጥ ሴቶችን በስራ በማሰማራት ከችግር እንዲወጡ ለማድረግ የነበራቸውን ውጥን እንዳስተጓጎለውም ነው የገለጹልኝ፡፡ የከተማ አስተዳደሩም እልባት ቢፈጥርላቸው የስራ ዕድል በመፍጠር አብሮ ለማደግ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
በወይዘሮ ተስፋነሽ በስኬታቸው ውስጥ የባለቤታቸው ድጋፍና አስተዋጽኦ ቀላል አለመሆኑን ያነሳሉ፡፡ ከቤት እንዲወጡ ደግፈዋቸዋልና፡፡ “ወጥቼ ስራ እንድሰራ የነበረኝን ፍርሃት ሰብሮልኛል” ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
ባለቤታቸው ሾፌር በመሆናቸው የሰው መኪና ይዘው ከሀገር ሀገር ይባዝኑ ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ ግን ወይዘሮ ተስፋነሽን ያሳስባቸው ነበር፡፡ መሪ የጨበጡ በመሆናቸው አደጋ ይከሰታል በሚል፡፡
ባለቤታቸው አሁን ለስራ ያዘጋጁትን የምርቶቻቸው መዳረሻ የማድረስ ተግባር እያከናወኑ መሆናቸው ስጋቶችን አስወግደዋል፡፡ መኪናውም ተጨማሪ አቅም ፈጥሮላቸዋል፡፡ ለስራቸው ቅልጥፍና ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ መኪና ከማሽከርከሩ ስራ ጎን ለጎንም ወይዘሮ ተስፋነሽ ገበያ ማፈላለግ ሲሰሩ ባለቤታቸው የስራውን አካባቢ ይቆጣጠራሉ፡፡ የማሽኖች የቴክኒክ ችግር ሲያጋጥምም በሙያቸው ችግሮቹን ይፈታሉ፡፡
ወይዘሮዋ ስራውን በማስፋት ወደ ትልቅ የግንባታ ኢንዱስትሪ የመቀየር ህልም አላቸው፡፡ ከብሎኬት ማምረቱ ጎን ለጎን የችፑድ፣ የቤትና የቢሮ እቃዎችን በዘመናዊ መንገድ ማምረት ነው ቀጣዩም ዕቅዳቸው፡፡ ለዚህም ተግባር የሚውሉ ማሽኖችን ማስገባት መጀመራቸውን ነው የተናገሩት፡፡
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ