የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን በማሳደግ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ የከተማው ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ገለፁ
የከተማው የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍና ተሳትፎ እንደሚያደርጉ የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር እንዳሉት በከተማው ከዚህ ቀደም ሲያጋጥም የነበረውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ዕቅድ በመንደፍ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው።
በአጭር ጊዜ ዕቅድ ውስጥ ከታቀዱ ተግባራት መካከልም የውሃ ስርጭት ፍትሃዊነት የማሻሻል እንዲሁም የተቋሙን ባለሙያና ስራ አመራር ኮሚቴ የማጠናከርና የአሰራር ስርዓትን የማሻሻል ስራዎች ከተቋቋመው ኢመርጀንሲ ቦርድ ጋር በመሆን በልዩ ትኩረት መከናወናቸውን አንስተዋል።
በዚህም ከቦዠባር የሚመጣው የውሃ መስመር የውሃ ብክነትን የመቀነስ፣ ህገ ወጥ ቅጥያን የማስቆም እና ህገወጥ ቆጣሪዎችን በአግባቡ የመቆጣጠር ስራ የአጎራባች መዋቅሮችን ጭምር በማሳተፍ በመሠራቱ በዘርፉ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የውሃ አቅምን የሚያሳድግ ፓምፕ ግዢ መፈጸሙን የተናገሩት ከንቲባው በዚህም ከዚህ ቀደም በሰከንድ ከ40 ሊትር በላይ ብቻ ዲስቻርጅ ወይም ይፈስ የነበረውን በሰከንድ እስከ 90 ሊትር ማሳደግ መቻሉንም ነው ያመላከቱት።
አያይዘውም አሁን ላይ በተለይም በቦዠባርና ጣጤሳ መስመሮች በስፋት ሲስተዋሉ የነበሩ ችግሮች መፍታት ተችሏል ያሉት አቶ ሙራድ በዚህም አንጻራዊ ለውጥ መምጣቱን ገልፀዋል።
የከተማው ውሃ ተቋም ባለሙያና አመራር ተግባራትን በሀላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ በውጤታማነት እንዲፈጽም በተሰራ ስራ በተለይም ውዝፍ ዕዳን ከማስከፈል፣ ህገ ወጥ ቆጣሪዎችና ቅጥያዎችን በመለየት ህጋዊ ከማድረግ እና ቆሻሻ የነበሩ ቆጣሪዎችን ከማጽዳት አንፃር ሰፊ ስራ መሠራቱን አንስተው በዚህም የተቋሙ ሰራተኞች ወርሃዊ ደመወዝና ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የአለም ባንክ ዕዳን መክፈል መቻሉን ጠቁመዋል።
ለዚህ ስኬታማነትም የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የከተማው ባለድርሻ አካላት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አቶ ሙራድ ተናግረዋል፡፡
አሁን በከተማው ፍትሃዊ የውሃ ስርጭት በፈረቃ እንዲከናወን መደረጉን ተከትሎ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እየታየ መምጣቱን በማመላከት የከተማው ህዝብ በተለይም ህገወጥነትን በመከላከል ረገድ ላበረከተው ድጋፍ አመስግነዋል።
የከተማው የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን በማሳደግ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው ተግባሩን ውጤታማ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴም ህዝቡን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍና ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከንቲባ ሙራድ ከድር ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ካነጋገርናቸው የከተማው ነዋሪዎች መካከል በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በከተማው ውሃ ለረጅም ጊዜ ይቋረጥ እንደነበር አውስተው አሁን ላይ ለውጥ መኖሩን ተናግረዋል።
የከተማው የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት በየደረጃው እየተደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና እንደ ነዋሪ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
ዘጋቢ፡ መሐመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ህብረት ስራ ማህበራት በተደራጁበት ዓላማ ለአባሎቻቸው የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በጠንካራ አደረጃጀትና ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ሊደገፉ እንደሚገባ ተመላከተ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር አክልሉ አዳኝ ማህበረሰቡን ከቱርካና ሐይቅና ከኦሞ ወንዝ ሙላት ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በስፍራው በመገኘት ተመለከቱ
የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በየደረጃዉ ለመመለስ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ አስታወቀ