ሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በ192 ሚሊዮን ብር ወጪ አዲስ የተቀናጀ የገጠር ልማት ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በሳውላ ከተማ አካሄደ
ፕሮጀከቱ የሚተገበረው በዞኑ ደምባ ጎፋ እና ዛላ ወረዳዎች ሲሆን ከ102 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።
የልማት ፕሮጀክቱ መሠረታዊ ችግሩን ጥናት አድርጎ ወደ ሥራ የገባ መሆኑን የጠቀሱት የሰዎች ለሰዎች ድርጅት አገር አቀፍ ተጠሪ አቶ ይልማ ታዬ፤ የመጀመሪያ ምዕራፍ በአጠቃላይ ለ3 አመታት በሚኖረው ቆይታ በ5 ዋና ዋና ዘርፎች ላይ በዘላቂ የመሬት ልማትና አጠቃቀም፣ በንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ንጽህና አጠባበቅ፣ በትምህርት፣ በጤና እና የሰው ሃብት ልማት ዘርፎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አብራርተዋል።
መድረኩ የመጀመሪያው ዙር የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን በዞኑ ሁለት ወረዳዎች ዛላና ደምባ ጎፋ ወረዳዎች ላይ ይጀመራል ብለዋል።
እንደ ነባራዊ ሁኔታው ተጠቃሚ ወረዳዎችንና የተያዘው በጀት የሚሰፋ መሆኑን የተናገሩት ተጠሪው፤ ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ እንዲገባ በዞኑ መንግስት ልዩ ልዩ ድጋፎች መደረጉን ገልጸዋል።
በጤናው ዘርፍ 15 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ለግል እና ማህበረሰብ ጤና አጠባበቅ፣ ለኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ስራዎች፣ ለቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶች እና የአቅም ግንባታ ስራዎች እንደሚሰሩ ተገልጿል።
የሰዎች ለሰዎች ድርጅት የፕሮጀክቶች ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ባህሪቱ ስዩም፤ በወረዳዎቹ ለሚገኙ ስድስት ጤና ተቋማት የጤና ቁሳቁስ፣ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ሰዎችም የዓይን ህክምና አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም ለእናቶችና ህጻናት ጤና ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት የታቀደ መሆኑን ገልጸዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ፤ እየተራቆተ የመጣውን የተፈጥሮ ሀብታችንን ዳግም እንዲያንሰራራ ለማስቻል ፕሮጀክቱ የሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም የተጀመረው ዕቅድ ስኬታማ እንዲሆን የዞኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ በዘላቂ የመሬት ልማትና አጠቃቀም ዘርፍ ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን ለመስራት ታቅዷል።
ከ300 ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት በደን ለመሸፈን ከ5 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በማፍላት ህብረተሰቡ እንዲተከልና አካባቢውን እንዲንከባከብ ይደረጋል ተብሏል።
ለውሃ እና ንጽህና ዘርፍ ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተመደበ ሲሆን፤ ሰባት መካከለኛ ጥልቀት ያላቸው ጉድጓድ ቁፋሮዎች እና አራት የምንጭ ማጎልበት ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የግል እና አካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ስልጠናዎችንም ለመስጠት መታቀዱ ተገልጿል::
ከተያዘው በጀት ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ በትምህርት ዘርፍ በዋናነትም የአንድ ትምህርት ቤት ግንባታ እና የትምህርት ግብዓቶች የማሟላት ስራ ይከናወናል፡፡
ከ180 በላይ ለሚሆኑ ሴቶችና ወጣቶች ሰራ ዕድል ፈጠራ እና የክህሎት ስልጠና፣ ከ1000 በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ ስልጠናና ተያያዥ ጉዳዮች 16 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቧል ተብሏል።
ተሳታፊዎችም ዞኑ በፕሮጀክቱ በመታቀፋቸው የተሠማቸውን ደስታ ገልጸው የተያዘው ዕቅድ ስኬታማ እንዲሆን የጋራ ርብርብ የሚሻ መሆኑን በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ ዶ/ር ቦሻ ቦምቤ በሰጡት የማጠቃለያ መልዕክት ክልሉን የሠላምና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ለተያዘው ዕቅድ ሰፊ ዕድል ይዞ የመጣ በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ያሳኩት የጋራ ድል መሆኑን የጨታ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ
በዶሮ እርባታ ስራ በመሰማራታቸው የገቢ ምንጫቸውን ከማሳደግ ባሻገር ለሌሎችም የሥራ እድል መፍጠር መቻላቸውን በአርባምንጭ ከተማ የሚገኙ ማህበራት ገለጹ
የክረምት ዝናብን ተከትሎ ጎርፍ እና መሰል አደጋዎች በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ