መንግሥት የወቅቱን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ያደረገው የደመወዝ ጭማሪ ተገቢ መሆኑን የሆሳዕና ከተማ የመንግሥት ሠራተኞች ገለጹ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 20/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) መንግሥት የወቅቱን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የወሰደው የደመወዝ ጭማሪ ማስተካከያ ተገቢ መሆኑን አንዳንድ በሆሳዕና ከተማ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ተናገሩ።
የደመወዝ ማሻሻያውን ምክንያት በማድረግ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ በማዕከላዊ አትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ አስታውቋል::
መንግስት ከመስከረም 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለመንግሥት ሠራተኛው ተጨማሪ የደመወዝ ማሻሻያ ለማድረግ መወሰኑ ይታወቃል፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡ አንዳንድ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት መንግሥት የሠራተኛውን ኑሮ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ነበራዊ ሁኔታ መሰረት ያደረገው የደመወዝ ማሻሻያ ለማድረግ በይፋ መግለጹ እንዳስደሰታቸው ጠቁመዋል።
ይህም ተግባራዊ ሲደረግ የመንግስት ሰራተኛው የኢኮኖሚ ጫና እንዲቀንስ እገዛው የላቀ እንደሆነም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩልም የመንግሥት ሠራተኛውም በተመደበበት የስራ ዘርፍ ውጤታማ ሆኖ አግልግሎት እንዲሰጥ ጭማሪው አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም በነበሩ ተመሳሳይ ወቅቶች አንዳንድ ራስ ወዳድ ነጋዴዎች የሰራተኛውን የደመወዝ ጭማሪ ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ የሆነ ጭማሪ እንዳደሚያደርጉ አስታውሰው፥ ይህ እንዳይደገም መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል።
የሀዲያ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀንቅስዶ ገብሬ እንደገለጹት፥ የደመወዝ ማሻሻያው መንግስት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የወሰደው እርምጃ ነው ብለዋል፡፡
የደመወዝ ማሻሻያ ውሳኔው ከንግድ ስርዓቱ ጋር ምንም የሚያገናኘው ጉዳይ እንደሌለ ጠቁመው፥ ምርትና አገልግሎት አቅራቢ ተቋማት በዚህ ሰበብ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ከማድረግ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
የዋጋ ለውጥን በመጠባበቅ ምርት በመደበቅ በገበያ ላይ እጥረት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይም አስተማሪ እርምጃ እንደሚወሰድ አቶ ሀንቅስዶ አሳውቀዋል::
ሸማቹ ህብረተሰብም አላስፈላጊ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ሲያጋጥሙ ለመንግሥት ጥቆማ በማድረስ ትብብር እንዲያደርግ ምክትል ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ: ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በሩብ ዓመቱ 3.7 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ወሰነች ቶማስ ገለጹ
የማር ምርት እጅግ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በጎምቦራ ወረዳ በንብ ማነብ ስራ የተሠማሩ አርሶአደሮች ተናገሩ
ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሰ የግብርና ልማት ላይ አደጋ እንዳያስከትል ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ተገለጸ