በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ480 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል – የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ480 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል – የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 20/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተያዘው የ2018 በጀት ዓመት ከ480 ሺህ በላይ ስራ አጥ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ በተከናወነው ቅንጅታዊ ስራ አበረታች ውጤት መመዝገቡም ተገልጿል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ከወልቂጤ ጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት፤ በክልሉ ስራ አጥ ዜጎችን በከተማና በገጠር በተለያዩ ዘርፎች እንዲደራጁ በማድረግ የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ዘርፈ ብዙ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

በዚህም በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጀምሮ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ነው የገለፁት።

የስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ በቅንጅት መሥራትን የሚጠይቅ መሆኑን በማንሳት ለዘርፉ ስኬታማነት በየደረጃው በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እያደረጉት ያለውን ድጋፍና ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በተለይም በግብርና ተኮር ዘላቂ የወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራም የሚሳተፈው አደይ ፕሮግራም በክልሉ በ15 ወረዳዎች ላይ እንደሚሰራና በተለይም ክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራን በማገዝ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ተግባሩ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ነው የገለፁት።

በበጀት ዓመቱ ከ371 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የተናገሩት አቶ ሙስጠፋ፤ ከእነዚህም አብዛኞቹ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዚህም ተጠቃሚነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

በዘርፉ ለተሰማሩ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር በዘለለ የመስሪያና መሸጫ ቦታ፣ የገበያና ብድር የማመቻቸት፣ የክህሎት ስልጠና እና ሌሎችም ድጋፎች መደረጋቸውን በማውሳት ብድር ከማስመለስ አንፃርም አበረታች ስራ መሠራቱንና ተግባሩ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

አሁን ላይ በነባር ኢንተርፕራይዞች፣ በግሉ ሴክተር፣ በቤተሰብ ደረጃ እንዲሁም በአዳዲስ ኢንሼቲቮች የስራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በተለይም በከተማ በኮሪደር ልማት፣ በወረዳ የአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት፣ በክልል ማዕከላት ቢሮ ህንፃዎች ግንባታ ላይ እንዲሁም በሌሎችም አማራጮች በመጠቀም የሥራ ዕድል ይፈጠራል ነው ያሉት ሀላፊው በማብራሪያቸው።

ለዚህም ውጤታማነት በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጠንካራ የድጋፍ እና ክትትል ስራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

በተያዘው የ2018 በጀት ዓመት በክልሉ ለ481 ሺህ 788 ስራ አጥ ዜጎች በገጠርና በከተማ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ግብ መጣሉን በመጥቀስ በዚህም ከ174 ሺህ በላይ ስራ አጥ ዜጎች በግብርና ዘርፍ እንደሚሰማሩ ሀላፊው አስታውቀዋል።

በበጀት ዓመቱ ጠንካራ ተቋምን በመገንባት፣ ዘላቂና አስተማማኝ የስራ ዕድልን መፍጠር እንዲሁም ኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።

በዘርፉ ለማከናወን የታቀዱ ተግባራት አብዛኞቹ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ለማከናወን የታቀደ ሲሆን ይህንን ተከትሎ በተከናወኑ ተግባራት በባለፈው ሐምሌ ወር ብቻ ለ10 ሺህ ስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም አቶ ሙስጠፋ አስረድተዋል።

እስከ ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም ድረስም የፖቴንሻልና የስራ ፈላጊ ልየታ ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚከናወን ነው ያመላከቱት።

በመሆኑም በክልሉ ያሉ ዕድሎችና ፀጋዎችን እንዲሁም ሌሎች አቅሞችን በመጠቀም የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ዘርፍን ውጤታማ በማድረግ የዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መደገፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ መሀመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን