በ2016 እና በ2017 ዓ.ም ከ4.5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ አደይ መንግስታዊ ፕሮግራም በአሪ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ ሥራ አጥ ወጣቶችን ወደ ሥራ እያስገባ መሆኑን አስታወቀ

በ2016 እና በ2017 ዓ.ም ከ4.5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ አደይ መንግስታዊ ፕሮግራም በአሪ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ ሥራ አጥ ወጣቶችን ወደ ሥራ እያስገባ መሆኑን አስታወቀ

በፕሮግራሙ በወረዳዉ በሁለት ዙር ከ1 ሺ 1 መቶ ለሚበልጡ ወጣቶች በሥራ እድል ፈጠራ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫና የክህሎት ሥልጠና ሰጥቷል።

አደይ ፕሮግራም ዓላማ አድርጎ የሚሠራዉ በግብርናዉ ዘርፍ ለወጣቶች ከግብዓት ማቅረብ ጀምሮ ምርቱን ለገበያ እስከማቅረብና ማቀነባበር የሚያስችል የሥራ መፍጠር እንደሆነ የተናገሩት በግብርና ትራንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ደቡብ ማዕከል አስተባባሪ አቶ በቀለ አይሸሽም ናቸዉ።

በ2016 እና በ2017 ዓ.ም ከ4.5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለእርባታና ለእርሻ ሥራ የሚሆኑ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ ሥራ አጥ ለሆኑ ወጣቶች አሥረክበዉ ወደ ሥራ ማስገባታቸዉንና በሁለት ዙር ከ1 ሺ 1 መቶ በላይ ለሚሆኑ ሥራ አጥ ወጣቶች የግንዛቤና የክህሎት ስልጠና መስጠታቸውን እንዲሁም በቀጣይ በወረዳው የተደራጁ ማህበራትን ዉጤታማ ለማድረግ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስተባባሪው ጥሪ አቅርበዋል።

የደቡብ አሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግዛዉ ሀይሌ በስልጠናው ወቅት ተገኝተዉ ባስተላለፉት መልእክት፤ የወቅቱን የኑሮ ውድነት ማሸነፍ የሚቻለዉ ከምንም በላይ ሠርቶ በመለወጥ ብቻ በመሆኑ ለዚህ ተግባር በስልጠናና ግብዓት በማቅረብ ድጋፍ እያደረገ ላለዉ የአደይ ፕሮጀክት ምስጋና አቅርበዋል።

ፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም ከ600 በላይ አሁን ከ450 በላይ የሚሆኑ ሥራ አጥ ወጣቶችን ያሰለጠነ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ የሥራ መነሳሳት መፍጠሩን ገልጸዉ፤ ቀጣይ በፕሮጀክት ለሚሠራዉ አጠቃላይ ተግባር አንደ ወረዳ አስተዳደር አስፈላጊዉን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸዉን ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ዙር ሥልጠና አግኝተው ከተደራጁ ማህበራት የነጋይ እንቁላል ዶሮ እርባታ ቁጥር ሁለት ኢንተርፕራይዝ ሰብሳቢ ሉቃስ ታሊሞስ፤ 200 እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በድጋፍ አግኝተው በቀን አስከ 150 እንቁላል በማግኘት ትርፋማ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግሯል።

ወጣት አስተዋይ አገኘሁወርቅ የሁለተኛ ዙር ሰልጣኝ ስትሆን በወተት ማቀነባበር ሥራ ዘርፍ ተሰማርታ ለመሥራት የሚያስችላትን የህይወት ክህሎትና በገንዘብ አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ በቂ ግንዛቤና ክህሎት ማግኘቷን ተናግራ፤ በተለይ የሴቶችን ችግር በመመልከት ሰፊውን ዕድል ለሴቶች በመስጠት አደይ ፕሮግራም ላደረገላቸዉ አበርክቶ አመስግናለች።

የአሪ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታፈሰ ተስፋዬ በበኩላቸዉ፤ በተፈጥሮ የተሰጠንን በቂ ሀብት በግንዛቤ ችግር ሀገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሻገር ባለመቻላችን አሁን የሚሰጠው ስልጠና ለመንግሥት ትልቅ አቅም ነዉ ብለዋል።

ቀጣይ ለሚኖረዉ ተግባር ከሴቶችና ህፃናት፣ ከወጣቶች፣ ከግብርና ሴክተሮችና ከሌሎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባር ለወጣቶቹ አስፈላጊውን ድጋፍ በሙሉ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፡ ራሔል አብራሃም – ከጂንካ ጣቢያችን