ቡናን በብዛትና በጥራት በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

ቡናን በብዛትና በጥራት በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 09/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ቡናን በብዛትና በጥራት በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባ የካፋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አጥናፉ ኃይሌ አስገነዘቡ።

ኃላፊዉ ይህንን ያሉት በዞኑ ቡና ጥራት ቁጥጥርና ግብይት ግብረ-ኃይል ንቅናቄ መድረክ ላይ ነው።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አጥናፉ ኃይሌ ቡና ከዞኑ ማህበረሰብ ታሪክ ጋር ቁርኝት ያለዉ መሆኑን ጠቁመዉ፥ ይህን ዕድል ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር በጥራትና በብዛት በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ከአልሚ ባለሀብቶች ጋር በመቀናጀት በቡና ልማት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ማረም ይገባል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካት የዘርፉ ባለሙያዎች የቡና ጥራትና ብዛት ላይ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የዞኑ ምክትል አስተዳደሪና የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ንጉሴ በ2018 ምርት ዘመን ከ20 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን ገልጸው ለዚህም ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በ2017 ዓመት የታዩ የአፈጻጸም ክፍተቶችን በአግባቡ በመለየት ለቀጣይ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራርን መከተል ይጠበቃል ብለዋል።

የዞኑ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋዎ አባመጫ፥ በዞኑ የቡና ልማት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዉ በተለይም አርሶ አደሩ ከግል ፍጆታና ከህገ-ወጥ ግብይት በመወጣት ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆን የግንዛቤ ስራ ይከናወናል ብለዋል።

ለዚህም የንቅናቄ መድረክ በየደረጃዉ እንደሚደረግ ገልጸው የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በመምሪያው የቡና፣ ሻይና ቅመማ-ቅመም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሞገስ ተክሌ ለንቅናቄ የተዘጋጀውን ሰነድ አቅርቧል።

በመጨረሻም በ2018 ዓመተ-ምህረት የዕቅድ ግብ ስምምነት የፊርማ ስነ-ስርዓት በማከናወን መድረኩ ተጠናቋል።

ዘጋቢ፡ ሀብታሙ ኃይሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን