በደቡብ ኦሞ ዞን ማሌ ወረዳ በ72 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ከኮይቤ ማቃና የ12 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የመንግድ ግንባታ ስራ ተጀመረ

በደቡብ ኦሞ ዞን ማሌ ወረዳ በ72 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ከኮይቤ ማቃና የ12 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የመንግድ ግንባታ ስራ ተጀመረ

ሀዋሳ፣ ነሐሴ 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኦሞ ዞን ማሌ ወረዳ ከኮይቤ ማቃና ድረስ ያለው 12 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የመንግድ ግንባታ ስራ ተጀመሯል፡፡

ህዝቡ የሚያነሳቸው የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን መንግስት ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ እና የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ ተናግረዋል፡፡

ከኮይቤ ማቃና የመንገድ ግንባታ ለረጅም ጊዜ የህዝቡ የመንገድ መሠረት ልማት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መደረጉን ገለጸው መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስና ያደሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በቁርጥኝነት እየሠራ ሲሆን አብዛኞቹ በተሰጠው ትኩረት ተጠናቀቅዋል ብለዋል።

በግንባታው ሂደት ህዝቡ ከተቋራጩ ጋር በመተባባርና በመደጋገፍ ሊሠሩ ይገባል ሲሉም አቶ ንጋቱ አሳስበዋል።

ከኮይቤ ማቃና የሚገነባው ደረጃውን የጠበቀ የጠጠር መንገድ 70 በመቶ በአለም ባንክ ቀሪው በክልል፣ በዞንና በወረዳ ወጪ በጀት እንደሚሸፍን ተገልጿል ።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ መንግስት የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ለመመለስ አቅዶ እየሠራ ነው ብለዋል።

ግንባታው የሚጀመረው ኮይቤ ማቃና የመንገድ ግንባታ በጥራትና በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ በሁሉ አቀፍ መልኩ መደገፍ አለበት ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።

የማሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አልጋጋ ባልንሴ እንደገለፁት ወረዳው ከፍተኛ የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር ያለበት መሆኑን ጠቅሰው ከኮይቤ ማቃና የሚገነባው የመንገድ መሠረተ ልማት ችግሩን በተወሰነ መልኩ ይፈታል ብለዋል።

የተጀመረው የመንገድ መሠረተ ልማት በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ የወረዳው አስተዳደር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትልና የዩራፕ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ዕድሌ ኢርኮ መንገድ ለእንድ አካባቢ ልማት ወሳኝ ነው ብለው ግንባታው ወደ ተግባር የሚገባው ኮይቤ ማቃና መንገድ ለዘመናት የህዝቡ ጥያቄ ሆኖ ቆይቶ ምላሽ ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡

በ72 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ኤልኮ የተሰኘ ተቋራጭ ውል ገብቶ መንገዱን ለመገንባት መረከቡን አቶ ዕድሌ ገልፀዋል።

የአካባቢው የጎሳ መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ለዘመናት ጥያቄ ሆኖ የሰነበተው መንገድ ወደ ሙሉ ግንባታ በመግባቱ ደስተኞች ስለመሆናቸው ገልፀዋል።

መንገዱ መገንባቱ ከዚህ በፊት ይቸገሩ የነበሩትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እንደሚፈታላቸውም ተናግረው ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ- ከጂንካ ጣቢያችን