በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ29 ሺህ በላይ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል

በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ29 ሺህ በላይ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል

ሀዋሳ፣ ነሐሴ 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ29 ሺህ በላይ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የዞኑ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ መምሪያ አስታውቋል፡፡

መምሪያው በ2017 ዓ.ም አፈጻጸምና በ2018 ዓ.ም ዕቅድ ዝግጅት ዙሪያ ሴክቶሪያል ጉባኤ አካሂዷል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ኢ/ር ዳግማዊ አየለ የተመዘገቡ ለውጦች ሙሉ ሆነው እንዲቀጥሉና የወጣቱን ተነሳሽነት ለመጨመር አስፈላጊው የድጋፍ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው በዚህም ብዙ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

በቀጣይም ደካማ ጎኖችን ገምግሞ በማረም የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ለሚደረገው ጥረት የባለ ድርሻ አካላት ድጋፍ አይነተኛ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸው በኢንደስትሪው ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ውስንነት የሚታይበት መሆኑን ገልጸዋል።

የተሠራጨን ብድር አስመልሶ በተዘዋዋሪ ለሥራ ፈላጊው ወጣት መልሶ በብድር ከማሰራጨት ረገድ በታችኛው መዋቅር ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየበት መሆኑን ተናግረው ነባር ዕዳን ከማሥመለስ አኳያ ግን ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ነው ብለዋል።

የወጣቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ካለፉት ጥቂት አመታት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ለውጥ የተመዘገበበት መሆኑን የጠቆሙት የዞኑ ም/አስተዳዳሪና የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ኋላፊ አቶ ምናሴ ኤልያስ ለዘርፉ የተሻለ ሀብት ከመመደብ አኳያም ልዩ ትኩረት የተሠጠው መሆኑን ገልጸዋል።

የመምሪያው ገጠር ዘርፍ ኋላፊ አቶ ተገኝ አበበ ባቀረቡት አፈጻጸም ሪፖርት በዞኑ ከተለዩ 35 ሺህ 438 ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ተለይተው በበጀት ዓመቱ በገጠርና በከተማ 19 ሺህ 62 ሥራ ፈላጊ ወጣቶችን በቋሚ የሥራ መሥኮች ማሠማራት መቻሉን አመላክተዋል።

በጊዜያዊ የሥራ መሥኮች ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ ሥምሪት ያገኙ ሲሆን በዞኑ እየተከናወኑ የሚገኙ የፌድራልና የክልል ልማታዊ ፕሮጀክቶች እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቃሷል።

በተጠናቀቀው በጀት አመት ባጠቃላይ ለ29 ሺህ 187 ሥራ ፈላጊ ወጣቶች በቋሚና በጊዜያዊ የሥራ ዕድል መሥኮች ተጠቃሚ መሆናቸውን አመላክተዋል።

በ2018 .ዓም በጀት አመትም 22 ሺህ 183 ሥራ ፈላጊ ወጣቶችን ለይቶ ወደ ሥራ ለማሠማራት ዕቅድ መያዙም ተመላክቷል፡፡

የተሳታፊ ባለድሻ አካላትና አመራሮች በተከናወኑ ተግባራት ላይና ዕቅዶች ዙሪያ ሀሳብ አስተያየት ተሰጥቶበታል።

በመጨረሻም በአፈጻጸም የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የእውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

ዘጋቢ፡ አወል ከድር