በኮንሶ ዞን በ2017 በጀት ዓመት ከ595 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ
የኮንሶ ዞን ገቢዎች መምሪያ በ2018 በጀት ዓመት 1 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱም ተመላክቷል።
መምሪያው በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና በ2018 ዕቅድ ላይ መክሯል።
አቶ ታምሩ ታደሰና ተስፋዬ ኩሲያ በኮንሶ ዞን የካራት ከተማ ግብር ከፋዮች ሲሆኑ ግብር ለሀገር ብልፅግና እና ለአካባቢ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስለሚያበረክት የሚጠበቅባቸውን ግብር በታማኝነትና በወቅቱ እንደሚከፍሉ ገልፀዋል።
በግብር አከፋፈል ስርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች መኖራቸውን ያልሸሸጉት ግብር ከፋዮቹ፤ በቀጣይ አሰራሮችን ከማዘመን ባለፈ አንዳንድ የስነ-ምግባር ችግሮ እንዲቀረፉ ጠይቀዋል።
በግምገማ መድረኩ የተገኙት የኮንሶ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ካሳሁን ገረመው፤ መምሪያው ከቀጥታ፣ ቀጥታ ካልሆኑ ታክሶችና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች እንዲሁም ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢዎች 586 ሚሊየን 822 ሺህ 483 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 595 ሚሊየን 943 ሺህ 455 ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ለንግዱ ማህበረሰብ በግብር ህጎችና ደንቦች ዙሪያ ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር ሆን ብለው ግብርን በሚሰውሩ አካላት ላይ የእርምት እርምጃ እየተወሰደ መቆየቱን አብራርተዋል።
የኮንሶ ዞን የመንግስት ተጠሪ አቶ ሀመር ሀንሻ በ2017 በጀት ዓመት አመራሩና በየደረጃው የሚገኘው አካል ለዕቅዱ ስኬት ቁርጠኛ እንደነበር ገልፀው፤ ገቢን በተሻለ ደረጃ ለመሰብሰብ በተደረገው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ በበጀት ዓመቱ የታቀደውን ገቢ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።
ዞኑ አሁንም የመልማት ጥያቄዎች ያለበት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሀመር፤ በቀጣይም ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የህብረተሰቡን የልማት ጥም ለማሳካት ቁርጠኛ መሆን ይጠበቃል ብለዋል።
የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገሌቦ ጎልትሞ፤ ግብር ለአካባቢ እድገትና ለውጥ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው በ2017 በጀት ዓመት የታዩ ክፍተቶችን በማረም በ2018 አንድ ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ የታቀደውን እቅድ ለማሳካት ሁሉም ቁርጠኛ መሆን አለበት ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ላቀድነው የ1 ቢሊየን ብር ገቢ ስኬት ሁሉም በሀላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ መስራት አንዳለበት አቶ ገሌቦ አሳስበው፤ ከስነ-ምግባር ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ አንዳንድ ክፍተቶች በቀጣይ ሊቀረፉ ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
ቡናን በብዛትና በጥራት በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ
በደቡብ ኦሞ ዞን ማሌ ወረዳ በ72 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ከኮይቤ ማቃና የ12 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የመንግድ ግንባታ ስራ ተጀመረ
በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ29 ሺህ በላይ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል