የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለዉ ተገለፀ

የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለዉ ተገለፀ

‎አካታች ስላምና ልማት በአፍሪካ (IPADA) የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በግብርና፣ በጤና፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና በሌሎች አገልግሎቶች ተሰማርቶ እየሰራ ያለዉ ስራ የሚበረታታና ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን የኣሪ ዞን አስታውቋል።

‎የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ እንደገለፁት፤ IPADA የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት ማህበረሰቡ ጤናው ተጠብቆ ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ በግብርናዉ ዘርፍ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣ በጤናው ዘርፍ ከማህበረሰቡ ተገልለዉ ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የነፃ ህክምና አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም የንፁህ መጠጥ ዉሃ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በአነስተኛ ወጪ ምንጭ የማጎልበት ስራዎችን ጨምሮ ሌሎች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ተስፋ የሚሰጡና ልምድ የሚወሰድባቸው ናቸው ብለዋል፡፡

‎IPADA ወይም አካታች ስላምና ልማት በአፍሪካ የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር ገብሬ ይንቲሶ በበኩላቸዉ፤ በግብርናዉ ዘርፍ የወተት ላም ዝርያ ማሻሻል፣ የመኖ ልማት እና የእንስሳት ክትባት አገልግሎት እንዲሁም በጤናዉ ዘርፍ ከአንገት በላይ ያሉ ህመሞች ህክምና ፊስቱላና የማህፀን ዉልቃት የቀዶ ጥገና ህክምናና የወባ በሽታ መከላከል ላይ እየሰሩ እንዳለ ገልፀዋል።

‎አክለውም የማህበረሰቡን የንፁህ መጠጥ ዉሃ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ምንጭ የማጎልበት ስራዎችን እና የከተማ ፅዳትና ውበት ስራዎች ላይ ተሰማርተው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‎የIPADA አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ፊሊፔ አይሻላ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከማህበረሰቡ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዉ፤ ዉጤታማ የሆኑ ስራዎችን ለመስራት የማህበረሰቡ የልማት ተነሳሽነትና ፍላጎት ወሳኝ በመሆኑ የተጀመሩ ስራዎች ዉጤታማ በመሆናቸዉ አጠናክሮ በማስቀጠል በቀጣይ በሌሎች የልማት ስራዎች ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡

‎የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ሚስጥሩ ሀምዳኪ፤ ድርጅቱ ከሆስፒታሉ ጋር በፈጠረው ስምምነት ከስፔይን ሀገር ሀኪሞችን በማስመጣት ለረጂም ጊዜ በህመም ሲሰቃዩ ለነበሩ የማህበረሰብ ክፍሎች 82 ከአንገት በላይ እባጭ እና እጢ ላለባቸዉ ታማሚዎች የቀዶ ጥገና ህክምና ከ140 በላይ የአይነ ሞራ ግርዶሾ ቀዶ ህክምና ለ14 እናቶች የማህጸን ዉልቃት ቀዶ ጥገና እና በወሊድ ምክንያት የሚከሰት የፊስቱላ ህክምና በሆስፒታሉ መሰጠቱን ገልፀዉ በወባ ወረርሽን መከላከል ላይም ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከታቸዉን ጠቅሰዋል፡፡

‎የኣሪ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የእንስሳት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስራት አበበ በበኩላቸዉ፤ ድርጅቱ በግብርናዉ ዘርፍ የወተት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ላይ በተካሄደዉ የሲንክሮናይዜሽን ዘመቻ አስፈላጊ የሆኑ ግበዓቶች ድጋፍ በማድረግ 2028 ከብቶችን በማዳቀል 63.3 በመቶ የሚሆኑ ከብቶች እርጉዝ መሆናቸው መረጋገጡንና አሁን ላይ እየወለዱ ያሉ ከብቶች መኖራቸውንም አስረድተዋል፡፡

‎የደቡብ ኣሪ ወረዳ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አጀለ ጌቱ ድርጅቱ 20 የምንጭ ማጎልበቻዎችን በመስራት ለማህበረሰቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት እየሰጠ በመሆኑ የወረዳውንም የውሃ ሽፋን 4 በመቶ ከፍ አድርጓል ብለዋል።

‎የድርጅቱ አስተባባሪ አቶ ኢሳያስ ጊዜያለው፤ የአርሶ አደሩን የመኖ እጥረት ለመቅረፍ በሰርቶ ማሳያ የተለያዩ አይነት ዝርያዎች እና ለከተማ ውበትና ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች እየለሙ እንደሆነና በዚህም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ገልፀዋል።

‎አስተያየታቸዉን ከሰጡን የአካባቢዉ ማህበረሰብ መካከል አቶ ማንተጋብቶት ነጋሽና ወ/ሮ አለሚቱ ሴቂሲ በጋራ በተደረገላቸው የማዳቀል ስራ ከብቶቻቸው እየወለዱ በሆናቸው ደስተኞች መሆናቸውን ገልፀው ፤ የተሰጣቸውን የተለያዩ አይነት የመኖ ዘሮችን እያለሙ ሲሆን ምርቱ ደርሶ ከብቶቹ መመገብ ሲጀምሩ ከወተት ምርቱም የተሻለ ጥቅም እንደሚያገኙም ተናግረዋል።

‎ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን