የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክን ተመራጭና የቱሪስት መዳረሻ ፓርክ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክን ተመራጭና የቱሪስት መዳረሻ ፓርክ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክን በሀገሪቱ ከሚገኙ ፓርኮች አንዱና ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ፓርክ ለማድረግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሠራተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ጽ/ቤት የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር አካሂደዋል።

የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን የሚገኝ ብቸኛ ፓርክ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ እንዳሉት የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክን ከመታደግ ወደ ማንሰራራት በሚል መሪ ቃል ፓርኩን ለማልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ፓርኩ የአካባቢውን ስነ ምህዳር ከመጠበቅ ባለፈ፥ በውስጡ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን በማልማት በቱሪዝሙ ዘርፍ ይበልጥ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ዲዛይን እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው፥ ፓርኩ ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ መሰረተ ልማት ለማሟላትና ማህበረሰብ ተኮር ሎጅ ለመገንባት በትብብር እየተሰራ ስለመሆኑም ለአካባቢው ባለሀብቶች በልማቱ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ተካ እንዳሉት 360 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ፓርኩ በውስጡም ብርቅዬ አእዋፋት፣ የዱር እንስሳትና በርካታ በስህቦች ይገኙበታል ብለዋል።

የክልሉ መንግስትና የጉራጌ ዞን አስተዳደር በሰጠው ልዩ ትኩረት ፓርኩ አሁን ላይ በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በችግኝ ተከላ መርሐግብሩ ከተሳተፉ አካላት መካከል የሚገኙት ፈዲላ ፈይዱ እና ስርጀባ ሰማን ለአካባቢ ጥበቃና ለተስተካከለ ስነ ምህዳር ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ አንጻር ችግኝ መትከሉ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ ላይ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ገመቹ አረቦ፣ የጉራጌ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ናስር ሀሰን፣ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።

ዘጋቢ፡ ተረፈ ሀብቴ – ከወልቂጤ ጣቢያችን