የቡና ምርጥ ዘርን በመጠቀም ምርታማነትን ማሣደግ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡና፣ ሻይና ቅመማ-ቅመም ባለስልጣን አሳሰበ

የቡና ምርጥ ዘርን በመጠቀም ምርታማነትን ማሣደግ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡና፣ ሻይና ቅመማ-ቅመም ባለስልጣን አሳሰበ

የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ-ቅመም ባለስልጣን ከክልሉ ግብርና ቢሮ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ጋር በመተባበርና ያዘጋጁት ስልጠና ለዞን፣ ለወረዳና ለቀበሌ ባለሙያዎች እንዲሁም ለቡና ዘር አዘጋጅ አርሶ-አደሮች የሚሰጥ ተግባር-ተኮር የአሰልጣኞች ስልጠና ነው፡፡

የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ-ቅመም ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተርና የልማትና ጥበቃ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይ ኮጁአብ ቡና ሰብል ብቻ ሳይሆን ከክልሉ ህዝብ ታሪክ፣ ባህልና ኢኮኖሚ ጋር ዘርፈ-ብዙ ትስስር ያለው ነው ብለዋል።

በመሆኑም በቡና ልማት ሥራ ውጤታማ ለመሆን በዘር ዝግጅት ላይ ሳይንስን በተከተለ መንገድ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የቡና ምርት ትመና ሥራን ለሀገር ኢኮኖሚ የሚኖረውን አስተዋፅኦ ባገናዘበ መንገድ መከወንና ተዓማኒነት ያለውን መረጃ መያዝ እንዲሁም ማስተላለፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ-ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ እስካሁን የነበሩ የቡና ዘር ዝግጅት ሥራዎች ላይ ጉድለት እንደሚታይ ገልጸው ጉድለቶችን በእውቀት ለማስተካከል ስልጠናው ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

ቡና ለረጅም ዓመታት ማሣ ላይ የሚቆይ ተክል በመሆኑ ምርጥ ዘርን በመጠቀም ምርታማነትን ማሣደግና የኢኮኖሚ ጠቀሜታውን እንዲሁም የምርጥ ዘሩን ምንጭ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በስልጠናው ከቀበሌ እስከ ክልል የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎችና የስራ ኃላፋዎች እንዲሁም የቡና ዘር አዘጋጅ አርሶ-አደሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ