የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የከተማውን የገበያ ዋጋ በማረጋጋት ረገድ ያበረከተው አስተዋዕጾ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የከተማውን የገበያ ዋጋ በማረጋጋት ረገድ ያበረከተው አስተዋዕጾ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የተከናወኑ የገቢ ማመንጫ ስራዎች ከገቢ ምንጭነት ባለፈ የከተማውን የገበያ ዋጋ በማረጋጋት ረገድ የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነው ሲል የጂንካ ከተማ ምክርቤት አባላት ገለጹ።

በኣሪ ዞን የጂንካ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 13ኛ ዓመት 53ኛ መደበኛ ጉባኤውን በምክርቤቱ አደራሽ ሰሞኑን ያካሄደ ሲሆን፥ የምክር ቤት አባላት እና አስፈፃሚ የሴክተር ኃላፊዎች በከተማው አስተዳደር በመከናወን ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ተኮር የልማት ተግባራትን ምልክታ አድርገዋል።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን አንዱ የምልከታው አካል ሲሆን በከተማ አስተዳደሩ የተጀመሩ መሰረተ ልማት እና የተለያዩ ግንባታዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል ።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ ይትባረክ ለምክርቤት አባላት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የተቋማትን ተልዕኮ እና ተግባራት ለመረዳት እንዲሁም የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት እና አረዳድ ለመፍጠር ተቀራርቦ መስራቱ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው በሦስት ዋና ዋና ዘርፎች ላይ ትኩረት ማድረጉን ጠቁመው፥ በግብርና፣ ቱሪዝምና ሃገር በቀል እውቀት እንዲሁም በአግሮ-ፕሮሰሲንግ ላይ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ዮሐንስ አብራርተው፥ በምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት የሚገኙ መልካም ተሞክሮዎችን ወደ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው አካባቢዎች ለማስፋት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የጂንካ ከተማ አስተዳደር አቶ ሲሳይ ጋልሺ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው እየሰራቸው ያሉ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች ከመማር ማስተማር ስራ ባሻገር ለጂንካ ከተማም ይሁን በአጎራባች ዞኖች ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ልዩ ልዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ማየታቸው በቀጣይ በተለይም በግብርናው ዘርፍ ተሞክሮ ወስዶ ለመስራት እንደሚያስችል ገልፀዋል።

የገቢ ማመንጫ ማዕከላት፣ የግብርና ሰርቶ ማሳያ በተለይም በበቆሎ በሩዝ ፣ በወተት ላም፣ በዓሳ እርባታ፣ በንብ ማነብ የተጀመረው ለአከባቢው ማህበረሰብ እንደ ሞዴል መወሰድ ያለበት መሆኑን የምክርቤት አባላቱ አባላት ተናግረዋል።


ምልከታ የተደረገባቸው ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቁመው በተመለከቱት ነገር ደስተኛ መሆናቸውንና በቀጣይ በሰፊው ቢሰራባቸው ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ እንቅስቃሴዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።


ዘጋቢ፡ ጳውሎስ አሚገሮ – ከጂንካ ጣቢያችን