በመኸር እርሻ ከ48 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን እየሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለፀ

በመኸር እርሻ ከ48 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን እየሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለፀ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኣሪ ዞን በዘንድሮ መኸር እርሻ ከ48 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን አቅዶ እየሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

መምሪያው በ2017/2018 ዓ.ም በመኸር እርሻ የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችል የተሻሻለ የጤፍ ዘር ብዜት ሥራ ከክልሉ ምርጥ ዘር ድርጅት ጋር በመሆን በባካዳውላ አሪ ወረዳ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።

በሥፍራው ተገኝተው የብዜት ሥራውን ያስጀመሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምርጥ ዘር ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ግዛው፥ እንደሀገር የተከሰተውን የምርጥ ዘር እጥረት ለመቅረፍ ቢሮው በአጭር ጊዜ ውጤታማ ሥራ ማከናወኑን ተናግረው የዚሁ አካል የሆነው ክሮስ-37 የተሰኘ የጤፍ ምርጥ ዘር ብዜት እየተከናወነ እንዳለም አስረድተዋል።

የኣሪ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ እንደገለፁት በ2017/18 ዓ.ም በመኸር እርሻ ወቅት ከ48ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቴክኖሎጂ ለመዝራት መታቀዱን ተናግረው የዞኑን እምቅ አቅም በመጠቀም ለክልሉ የሚበቃ ምርጥ ዘር ብዜት ሥራዎችን ለማከናወን በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩን ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለማሻገር የሚደረገው ጥረት ያለ ምርጥ ዘር አይታሰብም ያሉት የባካዳውላ ኣሪ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳዊት ጌታቸው በመኸሩ እርሻ 18 ነጥብ 6 ሄክታር መሬት የጤፍ ምርጥ ዘር ብዜት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

አቶ ዳዊት አክለው ባለፈው አመት በመኸር የነበሩ ተሞክሮችን በማጠናከር ጉድለቶችን በማረም የሕብረተሰቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ዘንድሮ በልዩ ትኩረት ይሠራል ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል የሰብል አይነትን በመለየት አርሶአደሩን ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ሁለንተናዊ ድጋፍና ክትትል ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ የግብርና ባለሙያዎች ገልጸዋል።

ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮችም የግብርና ባለሙያዎችን ምክረሀሳብ በመከተል የግብርና ምርቶችን በኩታገጠም በቴክኖሎጂ እየዘሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን