የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቀ

ማህበሩ ለተጎጂዎች የአፕል ችግኝ ማሰራጨቱንም አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ሮቤል ኦርሳንጎ እንደገለጹት፤ ማህበሩ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ስልጠና በመስጠት የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በመቅረጽ በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ እየሰራ ይገኛል።

ተጎጂዎች ኑሮአቸውን እንዲያሻሽሉ አንድ ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ ከአካባቢው ስነ-ምህዳር ጋር ተስማሚ የሆነውን የአፕል ችግኝ ከጋሞ ዞን ጨንቻ ከተማ በማምጣት ለእያንዳንዱ አባወራና እማወራ 11 ችግኝ ማሰራጨቱን ገልጸዋል።

አቶ ሮቤል አክለውም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጨ 50 ወጣቶችን በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ማሰማራቱን አስረድተዋል።

ቀደም ሲል ማህበሩ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በበልግ የእርሻ ወቅት 157 ኩንታል ዩሪያ፣ 157 ኩንታል ዳፕ፣ 40 ኩንታል በቆሎ ምርጥ ዘር እንዲሁም 14 ኩንታል ቦሎቄ ምርጥ ዘር ለተጎጂዎች ማሰራጨቱን ገልጸው በዚህም የተሻለ ምርት እያመረቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ተጎጂዎቹ በግቢያቸው በሌማት ትሩፋት ስራዎች እንዲሰማሩ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሰብዓዊ ዲፕሎማሲና ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ሙሉዋስ አቲሳ በበኩላቸው፤ ማህበሩ አደጋው ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ ለተጎጂዎች አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ በማድረግ ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ መሆኑን በተግባር ሲያሳይ መቆየቱን ተናግረዋል።

በአደጋው የተፈናቀሉ 627 አባዎራዎች እና እማወራዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ማህበሩ የተለያዩ ሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመዋል።

ማህበሩ 296 መኖሪያ ቤቶችን ለተጎጂዎች እያስገነባ ሲሆን አስከአሁን 260 ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የጎፋ ዞን አስተባባሪ አቶ ኢያሱ ጣሰው በበኩላቸው፤ ማህበሩ አደጋው ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ ለተጎጂዎች በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፍ በማድረግ ተጎጂዎችን በማቋቋም ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ማህበሩ ከጀርመን ቀይ መስቀል ማህበርና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ሁለት የውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ አከናውኖ ለአገልግሎት ማብቃቱን አስረድተዋል።

ማህበሩ ተጎጂዎች በሚደረግላቸው ምግብ ነክ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ብቻ ፍላጎታቸውን ማሟላት ስለማይችሉ ለእያንዳንዱ አባወራና እማወራ በየወሩ 6 ሺህ 900 ብር ለሶስት ተከታታይ ጊዜ ክፍያ መፈጸሙን አንስተዋል።

ካነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ ገረመው ጋርዳ፣ አቶ ሀላፋ ሀሪንጎ እና ወ/ሮ እየሩሳለም ያዕቆብ ማህበሩ ላደረገላቸው ሁሉ አቀፍ ድጋፍ አመስግነው፤ የወሰዱትን የአፕል ችግኝ ተንከባክበው ለውጤት በማብቃት ኑሮአቸውን ለማሻሻል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን